ቀጥታ፡

የአገር ሉአላዊነት መከታና የህዝብ አለኝታ የሆነ ጠንካራ ህብረ-ብሄራዊ ሰራዊት የመገንባቱን ስራ ሁላችንም መደገፍ አለብን- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 9/2015(ኢዜአ):- የአገር ሉአላዊነት መከታና የህዝብ አለኝታ የሆነ ጠንካራ ህብረ-ብሄራዊ ሰራዊት የመገንባቱን ስራ ሁላችንም መደገፍና ማገዝ አለብን ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ ገለጹ።

የክልል ልዩ ኃይሎች አደረጃጀት ህጋዊ አለመሆን፣ በክልሎች መካከል እንደ ስጋት መተያየት እንዲሁም ችግሮችን በሃይል ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ ልዩ ሀይሉን መልሶ ለማደራጀት ማስገደዱ ተገልጿል።

የክልል ልዩ ኃይሎችን በፌዴራልና የክልል የጸጥታ ተቋማት የመልሶ ማደራጀት ስራን በሚመለከት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ጀነራሎች፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልል የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ከሁለት ቀናት በፊት ተገምግሟል።

በመድረኩም በሁሉም ክልሎች የመልሶ ማደራጀት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉ ተጠቅሶ ከሚያዚያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀትና መዋቅር የለም ሲሉ ፊልድ ማርሻሉ አረጋግጠዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ፤ በክልሎች ለአመታት የተደራጀው ልዩ ኃይል ከህገ መንግስቱ ውጭ ስለመሆኑ ይናገራሉ።

የልዩ ሃይል አደረጃጀትና አተገባበር በክልሎች ወጥነት ያልነበረውና በተመሳሳይ ህግና ደንብ የሚመራ እንዳልነበርም አስታውሰዋል።

የክልል ልዩ ኃይሎች የተገነቡበት መንገድ የሀገርና የህዝብን ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ ለጥቂት ፖለቲከኞች አገልጋይ የነበረበት አጋጣሚ የበዛ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የክልል ልዩ ሃይሎችን በፌዴራልና የክልል የጸጥታ ተቋማት የመልሶ ማደራጀት ስራ መከናወኑ በኢትዮጵያ ህብረ-ብሄራዊ ሰራዊት በመገንባት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ዶክተር መብራቱ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የጸጥታ መዋቅሩ በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስና ሚሊሻ ብቻ መወሰኑ ትክክለኛ አሰራር መሆኑን ተናግረዋል።

ዶክተር መብራቱ አክለውም የኢትዮጵያ የሉአላዊነት መከታና የህዝብ አለኝታ የሆነ ጠንካራ ህብረ- ብሄራዊ ሰራዊት የመገንባቱን ስራ ሁላችንም መደገፍና ማገዝ አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም