ቀጥታ፡

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 8/2015(ኢዜአ):- በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የአራተኛና የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳሉ።

በዚህም ኢትዮጵያ መድን ከወላይታ ዲቻ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይጫወታሉ።

ኢትዮጵያ መድን በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ36 ነጥብ 3ኛ እንዲሁም ወላይታ ዲቻ በ23 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ኢትዮጵያ መድን በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ወላይታ ዲቻ በበኩሉ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ በመለያየት ምንም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።


 

በሌላኛው የሊጉ መርሐ-ግብር መቻል ከፋሲል ከነማ ጋር ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

መቻል በ23 ነጥብ 10ኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን ፋሲል ከነማ በ24 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

መቻል በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት በማስተናገድ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ መቻል 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ለገጣፎ ለገዳዲና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም