የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 8/2015(ኢዜአ):- የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ለክርስትና እምነት ተከታዮች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ “ለመላው ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ” የሚል መልዕክት በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋንም እንዲሁ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።
አምባሳደሩ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት የመልካም ምኞት መልዕክት “መልካም የፋሲካ በዓል ለመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በሙሉ” ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ ኤምባሲ “የትንሳኤ በዓል ተስፋን፣ ይቅርታ ማድረግንና ሁለተኛ እድል መስጠትን በማሰብ የምናከብረው በዓል ነው” ሲል በትዊተር ገጹ ባሰፈረው የመልካም ምኞት መግለጫ አስታውቋል።
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮችም መልካም የትንሳኤ በዓል እንዲሆን ተመኝቷል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን “የትንሳኤ በዓል የአዲስ ሕይወትና አዲስ ተስፋ መግለጫ ነው” ሲሉ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
“በዚህ ብሩህ በዓል ለኢትዮጵያውያን ወንድሞቼና እህቶቼ ሁሉ ሰላምን ለመመኘት እወዳለሁ” ብለዋል።
“ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው” ያሉት አምባሳደሩ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሰላም እንዲሆን ምኞቴ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የትንሳኤ በዓል የሰላም፣ የደስታና ብልጽግና እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ የዴንማርክ ኤምባሲ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓል የደስታና የሀሴት እንዲሆን ምኞቱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የኢራን ኤምባሲ “የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ኤምባሲና ሰራተኞች ለመላው ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች መልካም የትንሳኤ በዓል እንዲሆንላችሁ ይመኛሉ” ሲል መልካም ምኞቱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የሜክሲኮ ኤምባሲ በበኩሉ “ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም የትንሳኤ በዓል እንመኛለን” ሲል የመልካም ምኞት መልዕክቱን አስተላልፏል።
አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ፓኪስታን፣ ስሪላንካና ኦስትሪያ ሌሎች የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን የገለጹ አገራት ናቸው።
የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል(ፋሲካ) ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ነው።