ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የሠራዊቱንና የሠራዊቱን አመራሮች ስም የሚያጎድፉ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል--የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት - ኢዜአ አማርኛ
ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የሠራዊቱንና የሠራዊቱን አመራሮች ስም የሚያጎድፉ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል--የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2015(ኢዜአ)፦ ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የመከላከያ ሠራዊቱንና የሠራዊቱን አመራሮች ስም የሚያጎድፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አሳሰበ፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፤ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ አንዳንድ አካላት ሆን ብለውና በተቀናጀ አግባብ በሀሰተኛ መረጃ የመከላከያ ሰራዊትን እና የአመራሮቹን ስም እያጎደፉ መሆኑን ለኢዜአ የተናገሩት፡፡
የእነዚህ ቡድኖች ዋነኛ ዓላማ የሠራዊቱን ስም በማጥፋትና በሀሰት በመፈረጅ እርስ በርሱ እንዳይተማመን ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ፈጽሞ ሊሳካ የማይችል እኩይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በሠራዊቱ እና መሪዎቹ መካከል ያለውን ጠንካራ የዕዝ ሰንሰለት ለማላላት ቀን ከሌት የጥፋት አጀንዳ እንደሚፈጥሩ የተናገሩት ኮሎኔል ጌትነት፤ የዚህ ተልዕኮ ዋነኛ ዓላማም ሀገር ማፍረስ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እነዚህ አካላት ሠራዊቱ ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን ጠብቆ የሀገር ህልውና ያስከበረበትን ሂደት ለማንኳሰስ እየሞከሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከድርጊታቸው በአፋጣኝ እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በአንድ እጅ ትጥቅ፤ በሌላ እጅ ደግሞ ፖለቲካ ይዞ መንቀሳቀስ አይቻልም ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት።
ህብረተሰቡ የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊትን ለመከፋፈል የሚጥሩ አካላት መኖራቸውን ተገንዝቦ፤ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ማንኛውንም ዋጋ ከፍሎ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስከበር ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።