ቀጥታ፡

ሕዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤን በዓል ሲያከብር አብሮነትንና መደጋገፍን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ ሚያዚያ 7/2015(ኢዜአ)፦ ሕዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤን በዓል ሲያከብር አብሮነትንና መደጋገፍን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ነገ የሚከበረውን የትንሳኤ በዓል በማስመልከት ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መልዕክት ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተባበሩና ከተደጋገፉ አስቸጋሪ ጊዜዎችንና ፈተናዎችን በመሻገር ከሚያልሙት ስኬት ላይ መድረስ የሁልጊዜም ታሪካዊ እሴታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህን የአባቶች የመተባበርና የመደጋገፍ ታሪዊ እሴት ሕዝበ ክርስቲያኑ በትንሳኤ በዓል አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኘው ሕዝበ ክርስቲያን በዓሉን ሲያከብር አብሮነቱንና አንድነቱን በማጠናከር ያለው የሌለውን በመደገፍ እንዲሁም በፍቅርና በአንድነት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

በዓሉን ሕዝብ ክርስቲያኑ ያለ ምንም ስጋት እንዲያከብር አስፈለጊው የጸጥታ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል።

የትንሳኤ በዓል ለክልሉና ለመላው የኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም