ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የግሎባል ሴኩሪቲ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኖ ተመረጠ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 7/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የግሎባል ሴኩሪቲ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኖ ተመረጠ

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የግሎባል ሴኩሪቲ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኖ የተመረጠው በቻይና ናንጂንግ ከተማ ሚያዚያ 3 እና 4 ቀን 2015 በተካሄደው የዓለም አቀፍ የህዝብ ደህንነት ትብብር ፎረም (Global public security Cooperation Forum) ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ብረሚካኤል የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት የተመራው ልዑካን ቡድን በቻይና ናንጂንግና ቤጂንግ ከተማ ሲደርስ ደማቅ ፖሊሳዊ አቀባበል ተደርጎለታል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ብረሚካኤል በዓለም አቀፍ የህዝብ ደህንነት ትብብር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ፎረም ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም የቴክኖሎጂ እድገት የዓለም አቀፋዊ ትስስር ከመፍጠሩም ባሻገር መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች እንዳለው ተናግረዋል።

የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከል የሚቻለው በጋራ በመስራት ሲሆን ኢትዮጵያ በአፍሪካ፣ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ እና በአለም አቀፍ ደረጃ የህዝቦችን ደህንነት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል።

አያይዘውም ፎረሙ የዓለም አቀፍ ግጭቶችንና ዋና መንስኤዎችን ለማስወገድ፣ የአለም አቀፍ ደህንነት አስተዳደርን ለማሻሻል እና የፀጥታ ማስከበር የጋራ ጥረቶችን ለማበረታታት እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማምጣት ያለመ ነው ብለዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ከቫለንሲ ኡርኪዛ የኢንተርፖል ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የብራዚል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር እና የዓለም አቀፍ የሕግ ትብብር ኃላፊ ጋር ባደረጉት የጎንዮሽ ውይይት አደገኛ ዕፅ ዝውውርን ለመከላከል የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈራረሙ ታውቋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ብረሚካኤል ሚያዝያ 5 ቀን 2015 . በቤጂንግ ተገኝተው  ከቻይና  መንግስት ምክር ቤት አባል እና የህዝብ ደህንነት ሚኒስትር ዋንግ ዢአሆንግ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የኢትዮጵያን እና የቻይናን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመዋጋት እና የፀጥታ አካላትን የህግ ማስከበር አቅምን በመገንባት ረገድ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ አብሮ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የቻይና ፖሊስ አዛዥና የህዝብ ደህንነት ሚኒስትር ዋንግ ዢአሆንግ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን  የወዳጅነት ትብብር ለማጠናከር ትልቅ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ቻይና የሁለቱን ሀገራት የህግ ማስከበርና የፀጥታ አጋርነት ለማጠናከር እንዲሁም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስን በሰው ኃይል የአቅም ግንባታ፣ ለቴክኖሎጂ እና ለፖሊስ ሥራ የሚያገለግሉ የተለያዩ ትጥቆችን በከፍተኛ ደረጃ ለማገዝ ቃል ገብተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሁለትዮሽ የህግ አስከባሪ ማዕከል (Bilateral law enforcement center) እንዲገነባ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች መስማማታቸውም ተጠቁሟል።

ለዚህም ጥናትና አስፈላጊው ዝግጅት ለማድረግ የጋራ ኮሚቴ እንዲደራጅ እንዲሁም የሁለቱ አቻ የፖሊስ ተቋማት የጋራ መግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም