ኢትዮጵያ፣ ጣልያን እና ሶማሊያ ያላቸውን የሶስትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ፣ ጣልያን እና ሶማሊያ ያላቸውን የሶስትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ፣ ጣልያን እና ሶማሊያ ያላቸውን የሶስትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂዮ ሜሎኒ እና ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይታቸው በዋናነት የአገራቱን የሶስትዮሸ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
ውይይቱን የተከታተሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም እንዳሉት፤ መሪዎቹ ከሶስትዮሸ በተጨማሪ በባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ ያላቸውን አጋርነት በማጠናከር ረገድ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአገራቱ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ መግለጻቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
በተጨማሪም በተለይ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካካል ያለው የኢኮኖሚና መሰረተ ልማት ትስስር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መምከራቸውን ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሊያ በተለይ በመንገድ መሰረተ ልማት ለመተሳሳር በሚያደርጉት ጥረት ላይ ጣልያን አጋር እንደምትሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂዮ ሜሎኒ መግለጻቸውን ሀላፊዋ አንስተዋል፡፡
ይህ ተግባራዊ በሚሆንበት ጉዳይ ላይ ቀጣይ ውይይቶች እንደሚኖሩም እንዲሁ፡፡
በሌላ መልኩ የጣልያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያና ሶማሊያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በሚሰማሩበት ጉዳይ ላይ መሪዎቹ መምከራቸውንም ገልጸዋል፡፡
የጣልያን ኩባንያዎች በተለይ በኢትዮጵያ በግብርና በቱሪዝምና ታዳሽ ሃይል ዘርፍ እንዲሰማሩ የጣሊያን መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂዮ ሜሎኒ የተናገሩት፡፡
በሶማሊያ ያለው አንጻራዊ ሰላም ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኑ በሶስትዮሽ ውይይት መድረኩ ላይ መነሳቱን የፕሬስ ሴክሪታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም ጠቁመዋል፡፡
የጣልያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባሉ ምቹ ሁኔታዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ይበልጥ እየተነቃቃ መሆኑንም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም ተናግረዋል፡፡