የኢትዮጵያውያን እና የዳያስፖራ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፎረም በዋሽንግተን ዲሲ ተካሄደ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 7/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች እና ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፎረም በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተካሄደ።

ሚያዚያ 5 ቀን 2015 በተካሄደው ፎረም መክፈቻ ላይ የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመጠቀም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው እንዲሰሩ መንግስት እስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል።

በአገራችን የተጀመረው ዘላቂ ሰላም የማስፈን ሂደት እንዳይቀለበስ በሙሉ ቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በትግበራ ላይ የሚገኘው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የግሉ ዘርፍ ጉልህ ሚና እንዲጫወት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው መንግስት አስቻይ የፖሊሲ ማዕቀፎችን በመዘርጋትና ውስን በሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች ብቻ ይሳተፋል።

በተለይም አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ባለሃብቶች ያካበቱትን ሀብት፣ ልምድ እና እውቀት ወደ አገራቸው ይዘው በመግባት በግል እና ከአገር ውስጥ ባለሃብቶች ጋር በመሆን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።


 

ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ባንኮች የሚሰጡት ብድር ዘጠና በመቶ የሚሆነው ለግል ዘርፉ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ አስታውቀዋል።

በአሜሪካ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ስለሺ በቀለ “በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሀገር ልማት፣ በገጽታ ግንባታ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በትህምርት፣ በጤና እና በሌሎች ዘርፎች የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና ከአገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡


 

በግልም ሆነ በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ በቢዝነስና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች ኤምባሲው በአገር ቤት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው አገራችን ለኢንቨስትሮች ምቹ እንደትሆን ተግባራዊ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንደተደረጉ ተናግረዋል።

ባለሃብቶች ከገበያ ዳሰሳ ጥናት፣ ከፈቃድ ማውጣት፣ በስራ ላይ እና ከዛም አልፎ የሚገጥሟቸውን የቢሮክራሲ እና ተያያዥ መሰናክሎች በፍጥነት እልባት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።


 

የተለያዩ አገራት ባለሃብቶችን ወደ አገራችን ለመሳብ እና መረጃዎችን በተገቢው መንገድ ለማሰራጨት ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በተሳታፊዎች በኩልም ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ቀርበው ምላሽ መሰጠቱን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም