የትንሣኤ በዓልን የተቸገሩትን በመርዳት በፍቅርና በአንድነት እናከብራለን ሲሉ የድሬዳዋ ክርስትና እምነት ተከታዮች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የትንሣኤ በዓልን የተቸገሩትን በመርዳት በፍቅርና በአንድነት እናከብራለን ሲሉ የድሬዳዋ ክርስትና እምነት ተከታዮች ገለጹ
ድሬዳዋ፣ ሚያዝያ 6 / 2015 (ኢዜአ) የትንሳኤ በዓልን የተቸገሩትን በመርዳት ከሌሎች ኃይማኖት ተከታዮች ጋር በመሆን የተቸገሩትን በመርዳት በፍቅርና በአንድነት እንደሚያከብሩ የድሬዳዋ ከተማ ክርስትና እምነት ተከታዮች ተናገሩ።
በከተማዋ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች የስቅለትን በዓል አክብረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የእምነቱ ተከታዮች እንደተናገሩት፤ መጪውን የትንሣኤ በዓል የተቸገሩትን ወገኖች በመደገፍ ከሌሎች እምነት ተከታዮችና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ማዕድ በማጋራት ያከብራሉ።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ ወይዘሮ ፀሐይ አብርሃም በዓሉን በፍቅር፣ በመደጋገፍ፣ በመረዳዳትና የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክር መንገድ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የድሬዳዋ ነዋሪዎች በእምነት፣ በብሔርና በሌላም ጉዳዮች ልዩነት ሳይፈጥሩ ያላቸውን በማካፈል በፍቅርና በመደጋገፍ እንደሚኖሩ ጠቅሰው፣ በመጪው በዓል ይህንኑ በመድገም አንድነታችንን በዘላቂነት መጠበቅ ይኖርብናል ብለዋል።
ሌላው የእምነቱ ተከታይ አቶ ደመላሽ በንቲ የትንሣኤን በአል የማከብረው የተቸገሩትን ወገኖችና ህፃናት በማብላትና በማልበስ ነው ብለዋል።
በዓላት ውብና ደማቅ የሚሆኑት፤ የግልና የመንግሥት እንቅስቃሴ ውጤት የሚያመጡት ለሰላም በመፀለይና ለሰላም መረጋገጥ ሁላችንም ኃላፊነታችንን ስንወጣ ነው በማለትም ተናግረዋል።
ወጣት ሙሉጌታ ጥበበ በበኩሉ ከእስልምና ኃይማኖት ተከታይ ጓደኞቹ ጋር በዓሉን ሰላምን በማስጠበቅ ለማክበር መዘጋጀቱን አስታውቋል።
''እኛ ወጣቶች የአካባቢውንና የአገራችንን ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ እንወጣለን'' ብሏል።
''መንግሥት የአገራችንን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ስራ ፍሬያማ የሚሆነው በእኛ በዜጎቿ ሲደገፍ ነው'' ያለችው ደግሞ ወጣት ናርዶስ በቀለ ናት።
የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች በፆም ወራት ችግረኞችን ለመደገፍና ሰላምን በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ ስናደርገው የነበረውን መደጋገፍ መቀጠል አለብን ብላለች።
ይህን አንድነትና ዘላቂ ሰላምን በመጠበቅ የትንሳኤና የኢድ አልፈጥር በዓላትን ከእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ጋር በህብረት ለማክበር ተዘጋጅተናል፤ ለተቸገሩት ወገኖችም ድጋፍ እናደርጋለን ብሏል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ ርዕሰ አድባራት ወገዳማት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል የቅኔና የመፅሐፍ መምህር ያሬድ ዘ ብሩክ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረን ትምህርት መሠረት በዓሉን በአንድነት፣ በፍቅርና በመደጋገፍ ማክበር ይገባናል ብለዋል።
በተለይ የተቸገሩትን በማብላትና በማልበስ፣ የታመሙትን በመጠየቅና በመንከባከብ በዓላትን ማሳለፍ ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።