ቀጥታ፡

የክርስቶስን ፍቅር እና ፍጹም ይቅር ባይነት የመተሳሰብና የአብሮነታችን ተምሳሌት ማድረግ ይገባናል--የእምነቱ አባቶች

አዲስ አበባ ሚያዚያ 6/2015(ኢዜአ)፦ የክርስቶስን ፍቅር እና ፍጹም ይቅር ባይነት የመተሳሰብና የአብሮነታችን ተምሳሌት ማድረግ ይገባናል ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ተናገሩ።

የስቅለት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለያዩ አድባራት የእምነቱ ስርዓት በሚያዘው መሰረት በጸሎትና በስግደት ተከብሯል።

የስቅለት በዓል ሥርዓት ከሚከበርባቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም አንዷ ስትሆን የበዓሉን አከባበር በማስመልከት ኢዜአ የእምነቱን አባቶች አነጋግሯል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የብጹዕ ፓትሪያርክ ልዩ ጸኃፊ መላከ ህይወት ቆሞስ አባ ኃይለገብርኤል፤ ቤተክርስቲያኗ የምታስበው የስግደት፣ የፀሎትና ምህላ መርሃ-ግብር ክርስቶስ ለሰው ልጆች ነፃ መውጣት የከፈለውን ዋጋ በማሰብ ነው ብለዋል።

በትዕምርተ መስቀሉም ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ታላቅ ፍቅርን የገለጠበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጽህፈት ቤት የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አባል ንቡረ ዕድ አባ ዮኃንስ፤ የክርስቶስ ትዕምርተ መስቀል ፍቅርን፣ አንድነትና ይቅር ባይነት የተገለጠበት የነፃነት ቀን እንደሆነ ተናግረዋል።


 

"የክርስቶስ መስቀል ለኢትዮጵያውያን ፍቅርና አንድነትን ያስተምረናል" ያሉት ደግሞ በመንበረ ፓትርያርክ ጽህፈት ቤት የቴሌቪዥን ክፍል ሰራተኞች አስተዳደር መላከ ጸኃይ ጸዳሉ ነጋሽ ናቸው።

ክርስቶስም ወደ ምድር መጥቶ የሰው ልጆችን የበደል ደብዳቤ በመቅደድ በስቅለቱ ምህረትና ድህነትን እንደሰጠም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የክርስቶስን ፍቅር እና ፍጹም ይቅር ባይነት የመተሳሰብና የአብሮነታችን ተምሳሌት አድርገን መቀጠል አለበን ብለዋል።

ኢትዮጵያውያንም "እኔ እንደወደድኳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ናት" የሚለውን የክርስቶስ ቅዱስ ቃል በመላበስ እርስ በእርስ መተሳሰብና መዋደድ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የከፈለውን የፍቅርና የይቅርታ ዋጋ በማሰብም ኢትዮጵያውያን በደል፣ ቂምና ቁርሾን በፍቅርና ይቅርታ መሻገር እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

ትንሳዔ የአንድነትና የመተጋገዝ በዓል በመሆኑ ያለው ለሌለው በማካፈል በዓሉን በደስታ ማሳለፍ አለበት ብለዋል።

የስቅለት በዓል በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሲከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ቀዳማዊ አቡነ ማቲያስ፣ ብጹዓን ሊቀ ጳጳሳት፣ አባቶች እና የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም