ቀጥታ፡

የትንሳዔ በዓልን ስናከብር የአገር አንድነትን በዕርቅ ዘላቂ ለማድረግ ቃል በመግባት መሆን አለበት- የእምነት አባቶች

አዲስ አበባ ሚያዚያ 6/2015(ኢዜአ)፦ የትንሳዔ በዓልን ስናከብር የአገር አንድነትን በዕርቅ ዘላቂ ለማድረግ ቃል በመግባት መሆን አለበት ሲሉ የእምነት አባቶች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ የትንሳዔ በዓልን አስመልክተው ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም የትንሳዔን በዓል ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት እና የአገር አንድነትን በዕርቅ ዘላቂ ለማድረግ ቃል በመግባት መሆን አለበት ብለዋል።

"የሰው ልጅ ንስሐ ገባ የምንለው ይከተለው የነበረውን ክፉ ተግባር ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጎ በመተው ወደ መልካም ተግባር ሲመለስ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን የመሰለ ጥሩ አርዓያ ያለው ንስሐ በሀገራችን በቅርቡ ሲፈጸም አይተናል ያሉት ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ይህን ያደረጉ ወገኖችን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናቸዋለን ብለዋል፡፡

በመሆኑም በዓሉን ስናከበር የተቸገሩትን በመርዳት የአገር አንድነትን በዕርቅ ዘላቂ ለማድረግ ቃል በመግባት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።


 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉን ስናከብር ለድሆችና ለአቅመ ደካሞች፣ በችግር ውስጥ ላሉ ሰዎች በመለገስ መሆን አለበት ብለዋል።

በተጨማሪም የጥላቻን ሐሳብና ንግግር በትንሳዔ የምስራች እንለውጠው በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።


 

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ-ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ በበኩላቸው፤ የወጣቶች የነገ ተስፋ ብሩህ የሚሆነው የአገር ሰላምና አንድነት ሲጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአገራችንና ለሕዝባችን ሰላም ቅድሚያ በመስጠት በጋራ እንስራ በማለትም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የእምነት አባቶቹ ምዕመኑ በዓሉን የተቸገሩትን በመርዳት እንዲያከብርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም