ለትንሳዔና የዒድ በዓላት በሚከናወን እርድ ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ለገበያ እንዲቀርብ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለትንሳዔና የዒድ በዓላት በሚከናወን እርድ ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ለገበያ እንዲቀርብ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 6/2015(ኢዜአ) ለትንሳዔና የዒድ በዓላት እርድ ሲከናወን ለቆዳና ሌጦ ጥራት ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ለገበያ እንዲቀርብ በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ጠየቀ።
ማዕከሉ በመጪዎቹ በዓላት ሕብረተሰቡ እርድ ሲፈጽም ለቆዳና ሌጦ ጥራት ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ለራስም ሆነ ለአገር ጥቅም መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሷል።
የኢንስቲትዩቱ የቆዳ ቴክኖሎጂ ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሚሻሞ ሞካሶ፤ የቆዳና ሌጦ ውጤቶች በሥራ ዕድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ጭምር ለአገር የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን ይናገራሉ።
ሆኖም በተለይ በበዓላት ወቅት በሚከናወን እርድ ለቆዳ ተገቢው ጥንቃቄ እየተደረገ ባለመሆኑ ለብልሽት እየተዳረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ሕብረተሰቡ በተለይ በበዓላት ወቅት እርድ ሲያካሂድ ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በቀጣይ ለሚከበሩት የፋሲካና የዒድ በዓላት እርድ ሲከናወን ለቆዳና ሌጦ ጥንቃቄ በማድረግ ለገበያ ማቅረብ ይገባል ነው ያሉት።
የቆዳ ፋብሪካዎች ምርቱን በቀጥታ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ሕብረተሰቡ የቆዳና ሌጦ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ የቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎች በዓመት ከ20 ሚሊዮን በላይ ጥሬ ቆዳና ሌጦ በግብአትነት እንደሚጠቀሙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ የቆዳ ጥራትን ጠብቆ ለገበያ በማቅረብ ለአገር ጥቅም ከማዋል ባለፈ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ለዘርፉ ልማት የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ተብሏል።