ለበዓል የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ካጋጠመ በፍጥነት ጥገና የሚያደርግ ግብረ-ኃይል ተዘጋጅቷል- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ለበዓል የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ካጋጠመ በፍጥነት ጥገና የሚያደርግ ግብረ-ኃይል ተዘጋጅቷል- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
አዲስ አበባ ሚያዚያ 6/2015 (ኢዜአ) ለበዓል የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር ካጋጠመ በፍጥነት ጥገና የሚያደርግ የባለሙያዎች ግብረ- ኃይል መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ።
የፋሲካና የዒድ አልፈጥር በዓላት በሚከበሩባቸው ቀናት ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ሊያጋጥም የሚችለውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመፍታት በቂ ዝግጅት መደረጉንም አገልግሎቱ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ታዬ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ለበዓላቱ አከባበር የኃይል መቆራረጥ ችግር እንዳይከሰት ቀደም ተብሎ የማስተካከያ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የኃይል መቆራረጥ ችግር ካጋጠመ እንኳን በአስቸኳይ ጥገና የሚያደርግ የባለሙያዎች ግብረ-ኃይል ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በበዓል ዋዜማና በእለቱ የደንበኞች የኃይል አጠቃቀም ከፍተኛ በመሆኑ የኃይል መቆራረጥ ችግርን ለመቀነስ ከዋዜማው ጀምሮ ከኤክስፖርትና ሲሚንቶ አምራቾች ውጭ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ሥርዓት (ግሪድ) የሚጠቀሙትን ኃይል ያቋርጣሉ ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ በማይበዛበት ጊዜ ማለትም ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት ሰዎች ሥራቸውን እንዲያከናውኑም አቶ መላኩ ጠይቀዋል።
ለኃይል ፍጆታ ካርድ የሚሞሉ ደንበኞችም በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተለያዩ ማዕከላት መሙላት ይችላሉ ብለዋል።