በ19ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በ19ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 6/2015 (ኢዜአ)፦ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሁለተኛ ቀን ውሎ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ድሬዳዋ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ይጫወታሉ።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ድሬዳዋ ከተማ በ28 ነጥብ ስምንተኛ እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ በ36 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ድሬዳዋ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል።
በአንጻሩ ባህር ዳር ከተማ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም።
ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ባህር ዳር ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ነጥቡን ወደ 39 ከፍ በማድረግ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን እስኪያደርግ ድረስ በነጥብ እኩል ይሆናል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር በሊጉ ያደረጉት ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ሀዲያ ሆሳዕና ከአርባ ምንጭ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና በ24 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን አርባ ምንጭ ከተማ በ21 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሀዲያ ሆሳዕና በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን አራት ጊዜ ተሸንፏል።
ተጋጣሚው አርባ ምንጭ ከተማ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር የሊጉ መርሐ-ግብር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ19ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ሃዋሳ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 3 ለ 2 ሲያሸንፍ ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።