ቀጥታ፡

አገራት የዲጂታል ሉዓላዊነታቸውን መጠበቅ ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል - አቶ ሰለሞን ሶካ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2015(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ምህዳር ተጠቃሚዎች ማደግን ተከትሎ ለከፍተኛ የዲጂታል ሉዓላዊነት አደጋ የተጋለጡ አገራት ከአደጋው ራሳቸዉን ለመጠበቅ ሊሰሩ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር(ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ተናገሩ።

የአፍሪካ - ሩሲያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፎረም በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በጉባኤው የኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ተሞክሮን አካፍለዋል።

 

ኢትዮጵያ በሳይበር ምህዳሩ ላይ ያለዉን መልካም አጋጣሚ ከመጠቀም ባሻገር የዲጂታል ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የዲጂታል ሉዓላዊነት ጥሰትና የሳይበር ጥቃትን ለመቀነስ በራሷ አቅም ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ ጥቅም ላይ እያዋለች መሆኑን ገልጸዋል።

አገራት የአምስተኛዉን ግዛት (ሳይበር) ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ ያነሱት አቶ ሰለሞን በሳይበር ቴክኖሎጂ ላይ ያላቸዉን ጥገኝነት በአግባቡ መፈተሽና ማስተካከል ይገባቸዋል ብለዋል።


 

ታዳጊ አገራት በሌሎች በተለይም ባደጉት አገራት ላይ ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ ጥገኝነት ውስጥ በመሆናቸው የዲጂታል ሉዓላዊነታቸዉ ለአደጋ እንዲጋለጥ ማድረጉን ነው አቶ ሰለሞን ያስረዱት።

የሳይበር ምህዳሩ ድንበር የለሽነት፣ ኢ-ተገማችነትና ተለዋዋጭነት ዘርፉን ውስብስብ እንዳደረገዉ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ አገራት በሳይበር ሉዓላዊነታቸው ላይ ያላቸውን ስጋት ለመቀነስ የራሳቸዉን የቴክኖሎጂ ምርቶች መታጠቅና ከዘመኑ ጋር አብሮ መዘመን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።


 

እንደ አፍሪካ ያሉ በሳይበር ቴክኖሎጂ ዘርፍ ወደ ኋላ የቀሩ አገራት ከፍተኛ የሚባል የዲጂታል ሉዓላዊነት አደጋ እንዳለባቸውና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ ካልቻሉ ብሔራዊ ጥቅማቸዉ ለአደጋ መጋለጡ እንደማይቀር አመልክተዋል።

አገራት የሳይበር ምህዳሩ ካለው ድንበር የለሽ ባህርይ የተነሳ ምህዳሩ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለመጠቀም የጋራ ስታንዳርዶችን፣ ፖሊሲዎችንና የትብብር ማዕቀፎችን በመቅረጽ ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም