ቀጥታ፡

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በተሰጣቸው አደረጃጀት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ


ደሴ ኢዜአ ሚያዚያ 5/2015...የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት አዲስ በተሰጣቸው የፀጥታ ማስከበር አደረጃጀትና ምደባ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን  አስታወቁ።

በደቡብ ወሎ ዞን በክልል ፖሊስ፤ በማረሚያ ቤት ፖሊስና በአድማ ብተና ልዩ ፖሊስ የተመደቡ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ወደ የተመደቡበት ወረዳ ዛሬ ተሸኝተዋል፡፡

የልዩ ኃይል አባል ረዳት ሳጅን አደም እንድሪስ የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍ ሲልም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በተሰጣቸው ተልዕኮ ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት ለዘላቂ ሰላምና አንድነት እንደያግዝ ልዩ ኃይሉን በአዲስ በማደራጀት ወደ ላቀ ሥርዓት ለማሳደግ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

አደረጃጀቱ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅና ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

"በተንኮለኞች ልዩ ኃይል ትጥቅ ሊፈታ ነው በሚል የሚናፈሰው ወሬ  መሰረተ-ቢስ ነው፤ ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው ወደ አማራ ክልል ማረሚያ ቤት ፖሊስ በመቀላቀላቸው ደስተኛ ነኝ" ብለዋል ረዳት ኮማንደሩ፡፡

ምክትል ኢንስፔክተር በለጠ ደስታ በበኩላቸው ''አዲሱ አደረጃጀት ለሕዝብና ለሀገር ብቻ ሳይሆን እኛንም የተሻለ ተጠቃሚ እንድንሆን ዕድል ፈጥሯል'' ብለዋል፡፡

''ቀደም ሲል ወደ ልዩ ኃይል የገባሁት የክልሉን ሕዝብ ሰላም ለመጠበቅ ነው፣ አሁንም ከቀረበልኝ ብዙ አማራጭ የክልል ፖሊስነትን መርጬ በመመደቤ ተደስቻለሁ'' ሲሉ ገልጸዋል፡፡

"ሴረኞች እንደሚያናፍሱት አደረጃጀቱ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላትን ትጥቅ አስፈትቶ ማፍረስ  አይደለም"፤ ይልቁንም ወደ ተሻለና የላቀ አደረጃጀት በመመደብ ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ ዕድል የሰጠ መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል።

"በአንዳንድ ፖለቲከኞች ሴራና ሐሰት ወሬ" የተደናገሩ ጓዶቻቸውም ወደ ሚመደቡበት አካባቢ ሄደው ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ ምክትል ኢንስፔክተር በለጠ ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባል  ኮንስታብል አልማዝ ተበጀ ስለ አደረጃጀቱ ከመወያየታችንና ግንዛቤ ከመጨበጣችን ባለፈ መከላከያን፣ ፌዴራል ፖሊስንና የክልል ፖሊስን መቀላቀል እንድምንችል ተገንዝበን ወደ የመርጥነው ቦታ ከእነ ትጥቃችን ገብተናል ሲሉ ገልጸዋል ፡፡

''አደረጃጀቱ እኛም የተሻለ ጥቅም እንዲኖረን ያደርጋል፣ በተፈለግን ጊዜ ግን ለማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ ነን'' ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ መሐመድ እንደገለጹት፤ አደረጃጀቱ ትጥቅ የማስፈታትና የመበተን ሳይሆን በአንድ ማዕከል ጠንካራ የፀጥታ መዋቅር መፍጠር ነው፡፡

በመሆኑም ወደ ዞናችን የተመደቡ የልዩ ኃይል አባላት ወደ መደበኛ ፖሊስ፤ ማረሚያ ቤት ፖሊስና አድማ ብተና እየተቀላቀሉ ወደ የተመደቡበት ወረዳ እየተሸኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አደረጃጀቱ ለዘላቂ ሰላምና አንድነት የላቀ ድርሻ ያለው በመሆኑ ሁሉም ለሴረኞች ወሬ ጆሮ ባለመስጠት  ሃሳቡን ተቀብሎ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም