ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለኢሳት ቴሌቪዥን የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/5015(ኢዜአ)፦ ኢሳት በህዝቦች አብሮነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ሃሰተኛ ዘገባዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠብ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።

ባለስልጣኑ ኢሳት ቴሌቪዥን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሚዛናዊነት የጎደላቸው፣ በተጨባጭ መረጃ ያልተረጋገጡ የህዝቦች መተማመንና አንድነትን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ በማቅረብ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/2013 የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ 1185/2012 እና የጋዜጠኝነት ስነምግባርን በመጣስ ላይ ይገኛል ብሏል።

ለአብነትም ጣቢያው የካቲት 23/2015ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ የዜጎችን ቤት በማፍረስ ግፍ መፈጸሙን ድምጻዊ መብሬ መንግስቴ ተናገረ፡ ድምጻዊው በዜጎች ላይ የተፈጸመው በደል ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት መሆኑን ገልጿል፣' የሚል ዜና የቀረበ መሆኑን ጠቅሶ በዘገባው የተጠቀሱ አካላት ሀሳብና አስተያየት ሳይካተት ድምዳሜ ላይ የደረሰ በመረጃ ያልተደገፈና ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ አስተላልፏል ነው ያለው፡፡

እንዲሁም መጋቢት 6/2015ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወደ ከተማው የሚገቡ ዜጎችን አስመልክቶ ያደረጉት ንግግር ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭና የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት የሚጥስ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ፤ የሚል መረጃ ማቅረቡን ጠቅሶ በዘገባው ‘የጫካ ፕሮጀክት አንድ ሚሊየን የሚጠጋ በጣም አቅመ ደካሞች የሚባሉ ዜጎች አፈናቅሏል፣ የቤት ፈረሳውን የሚመራውን ግብርሐይል ቤቶቹን ከማፍረስ ባሻገር የንብረት ዘረፋ ውስጥ ተሰማርተዋል የሚገድሉ፣ የሚዘርፉ እና የሚደበድቡ ሰዎች ናቸው እያስተዳደሩን ያለው ' የሚሉ በሰነድ ወይም በማስረጃ ያልተረጋገጡና የተቋማትን መልካም ስም የሚያጠፉ፤ ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎች በኢሳት ቴሌቪዥን መሰራጨቱንም ገልጿል።

መጋቢት 12/2015ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል መቂ ከተማ እድሜያቸው 18 አመት ያልሞላ ታዳጊዎች ለወታደራዊ ስልጠና እየተመለመሉ ነው ሲሉ ወላጆች ለኢሳት ገለጹ'' በሚል አርዕስተ ዜና ስር በከተማዋ ከክልሉ ተወላጆች ውጪ ያለ አካል እንዳይኖር የማድረግ እቅድ አለ፡ የሚል ዘገባ ቀርቧል ያለው ባለስልጣኑ፤ መረጃው ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ የተዓማኒነት(የምንጭ) ችግር የተስተዋለበት ምንጮቻችን ነገሩን ከማለት ውጪ የድርጊቱን እውነትነት ሊያረጋግጡ በሚያስችሉ ማስረጃዎች ያልተመላከቱና በህብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬና ስጋትን ሊፈጥር የሚችል ጥንቃቄ የጎደለው ዘገባ ነበር ብሏል።

መጋቢት 13/2015 ዓ.ም ጣቢያው አዲሱ የሸገር ከተማ አስተዳደር ምስረታን ምክንያት በማድረግ በተጠና እና ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በክልሉ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ማንነት የሌላቸው ዜጎችን ቤት ለይቶ እያፈረሰ እንዲሁም ከክልሉ እያስወጣ ስለመሆኑ የሚያስረዳ ዘገባ መቅረቡን አንስቶ ዘገባው የተነሳውን ርዕሰ ጉዳይ ትክክለኝነት ለማረጋገጥ ጥረት ያላደረገና በህዝቦች አብሮነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል የሚችል ዘገባ ማስተላለፉን ጠቅሷል።

መጋቢት 22/2015ዓ.ም ከኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን የተመለመሉ የአማርኛ አስተማሪዎች አዲስ አበባ መግባታቸው ተሰማ፡' በሚል ዘገባ ጣቢያው ትምህርት ቢሮ ሆነ ሌሎች ተገቢ አካላትን ሳያካትት በህብረተሰቡ ዘንድ ብዥታን ሊፈጥር የሚችል ኢ-ሚዛናዊ ዘገባ አቅርቧል ብሏል፡፡

ቴሌቪዥን ጣቢያው ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ከጋዜጠኝት ስነምግባርና መርህ ጋር የሚጣረሱ፧ ማህበራዊና ተቋማዊ ሃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ክፍተት ያለባቸውን ዘገባዎች በማሰራጨት የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/2013 አንቀጽ 68/1(ሀ)እና (ለ) ፕሮግራሞች ወይም ዜናዎችን የተለያዩ አመለካከቶችን በማንጸባረቅ አጠቃላይ ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ሚዛናዊ እና ከአድሎ የጸዱ አድርጎ ማቅረብ! የሚሰራጨው ፕሮግራም ወይም ዜና ይዘትና ምንጭን እውነተኛና ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አሰራጩ ሪፖርቱ ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በሚል የተቀመጡ ህጎችን ያላከበረ መሆኑ ጠቅሷል፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/2013 አንቀጽ 68/2(መ)(ሠ) የወንጀል ድርጊት እንዲፈጸም እና ሰላም እና ጸጥታ እንዲደፈርስ የሚቀሰቅስ መሆን የለበትም፤ በብሮድካስት አገልግሎት ለስርጭት የሚቀርብ ማንኛውም ፕሮግራም ወይም ዜና የማንኛውም ሰው ዘር ቋንቋ እና ብሄርን መሰረት በማድረግ እንዲጠላ ወይም እንዲገለል የሚቀሰቅስ መሆን የለበትም የሚሉትን ድንጋጌዎችን የጣሰ መሆኑንም ጠቅሷል።

የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ 1185/2012 አንቀጽ5 ማንኛውም ሰው የሀሰት መረጃን በአደባባይ፣ ስብሰባዎች በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ ተግባር ነው፡ የሚሉ ድንጋጌዎችንየጣሱ ዘገባዎች መስተዋሉንም አብራረቷል።

በመሆኑም ጣቢያው ሚዛናዊነት የጎደላቸውን ሀሰተኛ ዘገባዎችን በማሰራጨት በህዝቦች አብሮነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ መረጃዎችን ከማስተላለፍ እንዲቆጠብ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም