ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ድንበር ዘለል ወንጀልና ሽብርተኝነትን በመከላከል ለቀጣናው ሰላም እያከናወነች ያለውን ስራ አጠናክራ ትቀጥላለች - የኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ድንበር ዘለል ወንጀል እና ሽብርተኝነትን በመከላከል ለቀጣናው ሰላም እያከናወነች ያለውን ስራ አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድንበር ዘለል ወንጀሎችንና ሽብርትኝነትን ለመከላከል ለሶስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የምክክር መድረክ የኮሚቴዎች ስብሰባ አጠናቋል።

በመድረኩም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴን ጨምሮ የኅብረቱ አባል አገራት ወንጀል ምርመራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የፖሊስ አዛዦች ኅብረት የኮሚቴዎች ስብሰባም ድንበር ዘለል ወንጀሎችንና ሽብርትኝነትን በመከላከል የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል ምክክር እንደሆነ ተገልጿል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ፥ ምክክሩ በቀጣናው የሚታዩ ድንበር ዘለል የሰላምና ደህንነት ስጋቶችን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የአባል አገራቱን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ድንበር ዘለል ወንጀልና ሽብርተኝነትን በትብብር ለመቆጣጠር የሚስችሉ ምክረ ሃሳቦች በመድረኩ ቀርበው ምክክር እንደተደረገባቸው ተናግረዋል።

መድረኩም በፆታዊ፣ በሽብርተኝነት፣ በሳይበር እና የህግ መተላለፍ ወንጀሎችን የሚመለከቱ ምክረ ሃሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሰላምና ደህንነት ተቋማቶቿ ላይ የወሰደቻቸውን የለውጥ እርምጃዎች በማስገንዘብ የቀጣናው አገራት ተሞክሮ እንዲወስዱ ማድረግ እንደተቻለም አንስተዋል።

የወንጀል ስጋቶችን ለመከላከል እገዛ ከሚያደርጉ ተቋማት ጋር በመተባበር የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በሊቀ-መንበርነት በምትመራው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ሽብርተኝነት፣ ድንበር ዘለል የወንጀል ስጋቶችን ለመከላከል ለቀጣናው አገራት የምታደርገው ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።


 

በፌዴራል ፖሊስ የብሔራዊ ኢንተርፖልና ዓለም አቀፍ የፖሊስ ትብብር ዳይሬክተር ኮማንደር ጸጋዬ ኃይሌ፤ ኢትዮጵያ ከቀጣናው አገራትና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን ሽብርተኝነትና ድንበር ዘለል ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል ጠንካራ ስርዓት እየተከተለች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በቀጣናው የፖሊስ አዛዦች የምክክር መድረክ ኢትዮጵያ በህብረተሰብ ተሳትፎ እና ከጎረቤት አገራት ጋር በመተባባር የምታካሂደው የጸረ-ሽብር እና ድንበር ዘለል ወንጀል መከላከል ስራ ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ተሞክሮ መቅረቡን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ምክትል ኮሚሽነር ተሻለ ተሾመ፤ ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ በንድፈ ሃሳብና በተግባር የታነጸ የፖሊስ ሰራዊት እንዲኖራት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የቀጣናውን ሰላምና ደህንነነት ለማስጠበቅ በሚደረግ የአቅም ግንባታ ስራም ለደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ሩዋንዳ ያሉ የቀጣናው አገራት የፖሊስ አባላት በዲፕሎማና ዲግሪ መርሃ-ግብር አሰልጥኖ ማስመረቁን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ የመጡ የፖሊስ ሰራዊት አባላት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ-ግብር ስልጠና በመስጠት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት የኮሚቴዎች ስብሰባ ላይ ከቀጣናው አባል አገራት የተውጣጡ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊዎች መሳተፋቸው ተመላክቷል።

የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት አስራ አራት አባል አገራት ያሉት ሲሆን ኢትዮጵያም በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል አማካኝነት ኅብረቱን በሊቀ-መንበርነት እየመራች ትገኛለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም