ቀጥታ፡

ምእመኑ በጾም ወቅት ያሳየውን መረዳዳትና አብሮነት የዘወትር ተግባር አድርጎ ሊቀጥል ይገባል-የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2015(ኢዜአ)፦ ምእመኑ በጾም ወቅት ያሳየውን መረዳዳትና አብሮነት የዘወትር ተግባር አድርጎ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የዐቢይ ፆም፤ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በኩል ደግሞ የረመዳን ወርን በጾምና በጸሎት በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ።

የጾም ወቅት ሰው ራሱን ከስጋዊ መሻት አርቆ ለመንፈሳዊነት የሚያስገዛበት ሲሆን፤ በዚህ ወቅት እንደየሃይማኖቱ አስተምህሮ በጎ ምግባራት የሚከናወኑበትም ነው።

ጾም ፍቅርን በመቸር፣ በጎነትን በተግባር በመግለጥ፣ ያለው ለሌለው በማካፈልና በመተዛዘን የሚፈጸም መንፈሳዊ ተግባር ነው።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ-ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሃይማኖቶች በጎ ተግባራትና መንፈሳዊ ጸጋ እንደሚያቀዳጁ እነዚህም ዘወትራዊ መሆን እንዳለባቸው ያስተምራሉ ብለዋል።

የሃይማኖቱ ቅዱሳት መጻሕፍት እና ሊቃውንት ቸርነትን፣ ሰላምን፣ ይቅር ባይነትን፣ መረዳዳትን በአፅንኦት የሚያስተምሩት ተከታዮቻቸው በበጎ ምግባር እንዲቀረጹ በማለም መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በጾም ወቅት የነበረው የምእመኑ መረዳዳትና አብሮነት የዘወትር ተግባር ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ምእመናን በጾም ወቅት ያሳዩትን ልገሳ፣ በጎነት እና መልካም ተግባር ከጾም በኋላም አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

"በጎነት አጥር የለውም" ያሉት ቀሲስ ታጋይ፤ ሁሉም እርስ በርሱ እንዲተዛዘን፣ አብሮነቱን በማጠናከር ሁሉንም በይቅርታ ማለፍ ይገባል በማለትም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለአቅመ ደካሞች ፍቅርንና እንክብካቤን በመለገስ አብሮነትን ማጠንከር የዘወትር ተግባር እንዲሆን አስገንዝበዋል።

የአባቶችን ምክርና ተግሳፅ በማዳመጥ፣ ከእኩይ ተግባራት በመቆጠብ ምእመኑ መልካምነትን አብዝቶ እንዲያሳይም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም