ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና  ሰራተኞች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አደረጉ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/2015 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ ውይይት አድርገዋል።

“ድሎችን የማጽናትና ፈተናዎችን የመሻገር፤ ወቅታዊና ታሪካዊ ተልዕኮዎች” በሚል ርዕስ  ውይይቱ ተከናውኗል።

በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተዘጋጀ የውይይት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ የሚዲያ ተቋማት ኢትዮጵያ እያለፈችበት የምትገኘውን ለውጥ ለማጽናት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሕዝብ ትክክለኛ የሆነ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ አበክሮ መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

ሕብረ-ብሔራዊ በሆነችው ኢትዮጵያ ኢዜአ በሀገሪቱ በርካታ አከባቢዎች ካሉት ሰፊ ተደራሽነት አኳያ መረጃዎች በተጠናከረና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ወደ ሕብረተሰቡ የማድረስ ስራን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እያለፈችበት የምትገኘው ለውጥ በርካታ የፖለቲካ ነጋዴዎች ጉዞዋን ለመግታት እየሰሩ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦችንና አስተያየቶች በማስተናገድ ልዩነቶች የአንድነት እንጂ የግጭት መንስኤ እንዳይሆኑ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ ስራዎች ላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሉት ምክትል ዋና ስራ አፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ ለውጡ በፖለቲካ ረገድ ምህዳሩን ለማስፋት የምህረትና የይቅርታ እሳቤን በመያዝ አሳሪ ሕጎችን በመለወጥ እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማትን ነጻነትና አቅማቸውን መጠቀም እንዲችሉ እድል የፈጠረ ነው ብለዋል።

ኢኮኖሚውን  ከውድቀት ለመታደግ  አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግና የለውጥ አቅምን ለልማት በመጠቀም እንዲሁም ግንባታቸው ተጓተውና ቆመው የነበሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በማፋጠን ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ልማትና እድገት ከሚያጎለብቱ ስኬቶች መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የለውጡ ስኬት ማሳያ መካከል  ነው ብለዋል።

ከስኬት ባሻገር ለውጡ በበርካታ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች እየተፈተነ እንደሚገኝ በመጠቆም ለውጡን ለማስቀጠል ተግዳሮቶችን በጋራ መመከት እንደሚገባ ነው አቶ ተፈራ ያመለከቱት።

በዚህ ረገድ ኢዜአ የራሱን ሚና ለመወጣት በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።

በውይይት ላይ የተሳተፉ የተቋሙ  ባለሞያዎች በበኩላቸው በለውጥ ሂደት ውስጥ ያሉ ስኬቶችን ለማስቀጠል አገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ የይዘት ስራዎችን በመስራት ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ  እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም