ቀጥታ፡

የክልል ልዩ ኃይሎችን በፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ማደራጀት ያስፈለገው ጠላት ከሩቅ የሚፈራት አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ነው- ፌዴራል ፖሊስ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የክልል ልዩ ኃይሎችን በፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ማደራጀት ያስፈለገው ጠላት ከሩቅ የሚፈራት አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገለጸ፡፡

የክልል ልዩ ኃይሎች የተገነቡበት መንገድ የሀገርና ህዝብን ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ የፖለቲከኞች መጠቀሚያ እየሆነ መጥቷል ብሏል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ማዕከል ኢንተለጀንስ ዋና መምሪያ ኃላፊና የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል መልሶ ማደራጀትና ስታንዳርድ ጥናት ቡድን መሪ ረዳት ኮሚሽነር ሀብታሙ ካሳ፤ ለኢዜአ እንዳሉት የክልል ልዩ ኃይሎች አወቃቀር ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት የለውም ብለዋል፡፡

የ1997 ዓ.ም ብሄራዊ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ለማርገብ ክልሎች አድማ በታኝ ፖሊስ እንዲያቋቁሙ መደረጉን ረዳት ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል፡፡

የተቋቋመው አድማ በታኝ ኃይል የሰው ሀይል ብዛት፣ የሚታጠቀው መሳሪያና አደረጃጀት ምን መምሰል እንዳለበት በአሰራር ስላልተቀመጠ ክልሎች በራሳቸው መንገድ ተጨማሪ ኃይል በማሰልጠን ልዩ ሃይል ብለው መሰየማቸውንም ገልጸዋል፡፡

የክልሎች ልዩ ኃይል ተጠሪነቱም አንዳንዶች በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ወይም ፕሬዝዳንት አንዳንዶች ደግሞ በጸጥታ መዋቅሩ ስር እንዲሆን በማድረግ አደራጅተውታል ብለዋል፡፡

ፖሊስ 85 በመቶ ስራው ወንጀልን መከላከል መሆኑን የገለጹት ረዳት ኮሚሽነር ሀብታሙ፤ የክልል ልዩ ኃይሎች አደረጃጀት የመደበኛ ፖሊስን ተልዕኮ የሚያቀጭጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የክልል ልዩ ኃይሎች ከፖሊሳዊ ይልቅ ወታደራዊ ስልጠና ላይ ያተኮረ በመሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች መጠቀሚያ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ህብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀች ጠላቶቿ ከሩቅ የሚፈሯት ኢትዮጵያን ለመገንባት የጸጥታ ኃይሉ እንዴት ይደራጅ በሚለው ላይ አምስት ዓመት የፈጀ ጥናት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ጥናቱ ሲደረግ እንደ ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓትና ህብረ ብሔራዊ አወቃቀር ያላቸው ሀገራት ልምድ መወሰዱን የገለጹት ረዳት ኮሚሽነር ሀብታሙ፤ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት በዓለም ላይ የሌለ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

በተለያየ ማንነት የተገነባ ህዝብ ያላቸው የናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም የህንድ ተሞክሮ እንደሚያሳየው በማዕከላዊ መንግስት የሚታዘዝ እንጂ በክልል የሚተዳደር ልዩ ኃይል የለም ብለዋል፡፡

አሁን ያለው የክልል የጸጥታ ኃይሎች አደረጃጀት ኢትዮጵያን ወደ ትርምስ እንጂ ወደ ልማት አይወስዳትም፤ የኢትዮጵያ ህዝብም እንደገና ማደራጀቱን እንደሚደግፈው ባደረግነው የዳሰሳ ጥናት አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

በጥናቱ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ፕሬዝዳንቶች፣ የጸጥታ ተቋማት፣ መከላከያ እስከ ወረዳ ያሉ የክልል ልዩ ኃይል አመራሮችና አሀዶች ጥልቅ ውይይት አድርገው በአተገባበሩ ላይም ተስማምተውበት የተጀመረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ጠላት ቢመጣ አንድነቱ የተጠበቀ ኃይል እንደሚያስፈልጋት የገለጹት ረዳት ኮሚሽነር ሀብታሙ፤ ለተለያየ አላማ ቃለ መሀላ የፈጸመ የክልል ልዩ ኃይል ሊታደጋት አይችልም ብለዋል፡፡

የክልል ልዩ ኃይሎች ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግስት በመሆኑ ለልዩ ኃይል ብቻ በዓመት እስከ 9 ቢሊዮን ብር ፈሰስ የሚያደርጉ ክልሎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ በ2022 ከአፍሪካ ምርጥ አምስት ተቋማት አንዱ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት መስፈርቱን የሚያሟሉ የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀቱ ስራ በአብዛኞቹ ክልሎች በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም ረዳት ኮሚሽነር ሀብታሙ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም