ቀጥታ፡

የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት የተጀመረው ሥራ ጠንካራ ሕብረ-ብሔራዊ ሠራዊት ለመገንባት ያግዛል- ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ኃብተማርያም

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/2015 (ኢዜአ)፦ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት የተጀመረው ሥራ ጠንካራ ሕብረ-ብሔራዊ ሰራዊት ለመገንባት እንደሚያግዝ የቀድሞ ሠራዊት አባል ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ኃብተማርያም ተናገሩ።

ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ኃብተማርያም የቀድሞው የአየር ወለድ ኮማንዶ አዛዥ የነበሩ ሲሆን ከአሰልጣኝነት እስከ አዛዥነት ለ40 ዓመታት አገራቸውን አገልግለዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የተሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት በመወጣታቸው "ወደር የሌለው የኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ጀግና የጦር ሜዳይ" ሽልማትን አግኝተዋል።

በተለይ በ1970 ዓ.ም በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት በጠላት ቀለበት ውስጥ የነበሩትን ሐረርና ድሬደዋን ለማስለቀቅ ከጓዶቻቸው ጋር ሆነው ታላቅ ጀብዱ ፈጽመዋል፡፡

ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ኃብተማርያም፤ በአሁኑ ወቅት በወታደራዊ ሳይንስ የሰለጠነ፣ በስነ-ምግባር የታነጸ እንዲሁም ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ ጠንካራ ሠራዊት ለመገንባት እየተከናወነ ያለው ሥራ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት የተጀመረው ሥራ እንደ አገር ጠንካራ ሠራዊት ለመገንባት እንደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡

የክልሎች ልዩ ኃይሎች በሥልጠና ያገኙትን እውቀትና በተግባር ያካበቱትን ልምድ ይዘው በምርጫቸው ሠራዊቱን ሲቀላቀሉ ጠንካራ ሕብረ-ብሔራዊ ኃይል ለመገንባት የተጀመረውን ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል።

መንግሥት ያቀረበው አማራጭ የክልሎች ልዩ ኃይል አገር ችግር በገጠማት ወቅት ከሠራዊቱ ጋር ለከፈሉት ዋጋ ክብር የሚሰጥ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በወታደራዊ ሳይንስ ውስጥ "ልዩ ኃይል" ወይም "ስፔሻል ፎርስ" ተብሎ የሚጠራው የተለየ ሥልጠና የወሰደና የተለየ እውቀት ያለው እንዲሁም የሚሰጠውን ልዩ ግዳጅ በብቃት የሚፈጽም መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ኃይል ሊደራጅ የሚገባው ደግሞ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም