ቀጥታ፡

ጸሎተ ሐሙስ  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በድምቀት ተከበረ 

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2015 (ኢዜአ)፦ የትህትና መገለጫ የሆነው የጸሎተ ሐሙስ መታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በድምቀት ተከብሯል፡፡

ጸሎተ ሐሙስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በርካታ ስያሜዎች አሉት፡፡

በቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ መሰረት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ መኾኑን ለመግለጽና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ቀን ነውና ‹ጸሎተ ሐሙስ› ይባላል፡፡ 


 

ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ ያጠበበትን ለማስታወስም ‹ሕጽበተ ሐሙስ› የሚል ስያሜ አለው፡፡

በዚህም እለቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና አማኞች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡

የቤተክርስቲያኗ ሊቃነ-ጳጳሳትና ቀሳውስት " በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ፤ እኛም የአንተን አርዓያነት ተከትለን የልጆቻችንን እግር እናጥባለን።" ሲሉ በቤተክርስቲያን የተገኙ ምእመናንን እግር  በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

በዛሬው እለትም ይህን ለማስታወስ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የቤተክርስቲያኗ  ጳጳሳት፣ ካህናት እና ምእመናን በተገኙበት በመንበረ-ፓትሪያርክ  ቅድስተ ቅዱሳን  ማርያም ገዳም ቤተክርስቲያን ጸሎት፣ ቅዳሴና ስግደት ተካሂዷል።

በዚህም የኢየሱስ ክርስቶስን ትህትናና አክብሮት ለማሳየት በቤተክርስቲያኗ ሕጽበት ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን ጨምሮ ጳጳሳት የሕጽበት ሥነ-ሥርዓቱን አከናውነዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም