11ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን የባለድርሻ አካላት ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
11ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን የባለድርሻ አካላት ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2015(ኢዜአ)፦ 11ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን የባለድርሻ አካላት ጉባኤ ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 1/2015 በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ጉባኤው “የአፍሪካ የአቪዬሽን ትርክት መቀየር” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከናወን ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ጉባኤውን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በአፍሪካ የአቪዬሽን ዘርፉ በሚጠበቀው ልክ አለማደጉንና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዘርፉ ላይ ተጨማሪ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሮ መቆየቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል።
የአፍሪካ አቪዬሽን የባለድርሻ አካላት ጉባኤ በዘርፉ እያጋጠሙ ባሉ ተግዳሮቶች ላይ ለመምከር መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ዋና ጸሀፊ አብዱራህማን በርቴ በበኩላቸው የአፍሪካ አቪዬሽን ዘርፍ ገና በመነቃቃት ላይ በመሆኑ ጉባኤው ዘርፉን ወደ ላቀ ከፍታ ለማምጣት ምክክር እንደሚደረግበት ገልጸዋል።
በ11ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን የባለድርሻ አካላት ጉባኤ ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ የዘርፉ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
10ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን የባለድርሻ አካላት ጉባኤ እ.አ.አ ግንቦት 2022 በኬንያ ናይሮቢ መካሄዱ የሚታወስ ነው።