ቀጥታ፡

በመዲናዋ የትንሳኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል-ከተማ አስተዳደሩ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2015(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የትንሳኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፣የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለበዓላቱ የተደረጉ ዝግጅቶችን በሚመለከት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ፤  የትንሳኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት በደመቀ መልኩ እንዲያከብሩ በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት  የቅድመ ዝግጅት ስራ  ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመጪው  እሁድ ለሚከበረው የትንሳኤ በዓል ለህብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ ስጋ ለማቅረብ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት  በተሽከርካሪና በባለሙያ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

የውሀ አቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር ይሰራል ያሉት ምክትል ስራ አስኪያጁ፤ ለሚፈጠሩ ችግርች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ እና አስፈላጊውን ጥገና የሚያደርግ ቡድን ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ ከበዓሉ አከባበር ጋር ተያይዞ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ለከተማዋ ጽዳት የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አቶ ፍሰሐ ጋረደው በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡ የተለያዩ ምግቦችን ለማብሰል የሚጠቀማቸውን የኤሌክትሪክና ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች ሲጠቀም አደጋ በማይፈጥር መልኩ እንዲሆን የግንዛቤ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ሲያጋጥሙ የመቆጣጠር ስራ ለመስራት ከ500 በላይ የአደጋ ተከላካይ ሰራተኞች፣ 39 አምቡላንሶች ተቋሙ ሉት ቅርንጫፎች ዝግጁ  መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ኮሚሽነሩ አያየዘውም በዓላት በሚኖሩበት ወቅት ህብረተሰቡ ከፍተኛ ኃይል የመጠቀም ፍላጎት እንደሚጨምር አንስተው ከዚህ ጋር ተያይዞ ማንኛውም አደጋ  ሲከሰት በ939 በመደወል ማሳወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ገበየሁ ሊካሳ በበኩላቸው የኃይል መቆራረጥ እንዳይፈጠር ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፤ ከተፈጠረም አስፈላጊውን ጥገና ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም