የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት በአዲስ መልክ መደራጀታቸው በከፍተኛ የህዝብ ፍቅር ሲያከናወኑት የቆዩትን ፖሊሳዊ አገልግሎት እንዲያጠናክሩ የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት በአዲስ መልክ መደራጀታቸው በከፍተኛ የህዝብ ፍቅር ሲያከናወኑት የቆዩትን ፖሊሳዊ አገልግሎት እንዲያጠናክሩ የሚያስችል ነው
ጅግጂጋ ሚያዚያ 4/2015 (ኢዜአ )የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በአዲስ መልክ መደራጀታቸው እስካሁን በከፍተኛ የህዝብ ፍቅር ሲያከናወኑት የቆዩትን ፖሊሳዊ አገልግሎት እንዲያጠክናሩ የሚያስችል ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ማምሻውን ከክልሉ ልዩ ኃይል አመራሮችና አባላት ጋር በመንግሥት የተቀመጠውን የሁሉንም ክልሎች ልዩ ኃይል አባላት በአዲስ አደረጃጀት ለማጠናከር ስለሚኖረው ጠቀሜታና አተገባበሩ ዙሪያ ተወያይተዋል።
የልዩ ኃይል አባላት አዲሱ አደረጃጀት በተለያየ መልኩ እስካሁን ያላገኙትን መብቶች እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ሆኖ የተቀረፀ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።
በክልሉ የልዩ ኃይል አባላትን በአዲስ መልክ ለማደራጀትና ለማጠናከር የታሰበውን አገልግሎት ለማደናቀፍ በማሰብ "ልዩ ኃይሉ ሊፈርስ ነው በሚል የሚነዛው ወሬ መሰረተ-ቢስ ነው" ብለዋል።
"የልዩ ኃይል አባላት በአዲስ መልክ መደራጀታቸው እስካሁን በከፍተኛ የህዝብ ፍቅር ሲያከናወኑት የቆየትን ፖሊሳዊ አገልግሎት እንዲያጠናክሩ የሚያስችላቸው ነው" ሲሉ በአፅንኦት ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የልዩ ኃይል አባላት ስለአዲሱ አደረጃጀትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ የስራ ኃላፊዎች፣ የልዩ ኃይሉ አመራሮችና አባላት የተገኙ ሲሆን ከመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎች በርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።