ቀጥታ፡

 አደንዛዥ እጽ ለመከላከል አገራዊ ገለልተኛ ተቋም ሊደራጅ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 04/2015(ኢዜአ)፦ ወጣቱን ትውልድ ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚዳርጉ አደንዛዥ እጾችን ለመከላከል ራሱን የቻለ አገራዊ ገለልተኛ ተቋም ማደራጀት እንደሚገባ ተገለጸ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቀጣይ አንድ ዓመት የሚተገበር የፀረ-አደንዛዥ እጾች የንቅናቄ መድረክ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት  በተገኙበት ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።

'ኢትዮ ከሱስ የነጻ ትውልድ' የተሰኘ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ጃራ ሰማ የአደንዛዥ እጽ ምርትና አቅርቦት መጨመር በተለይ የወጣቶች ተጋላጭነት እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል።

በመሆኑም አስገዳጅ ሕግ በማውጣትና ከመንግስትና ከግል ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ገለልተኛ አገራዊ ተቋም በማደራጀት በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።


 

'ሪዴም ዘ ጀኔሬሽን' የተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ስብሐት በበኩላቸው የወጣቶች ስብእና ግንባታ ላይ አትኩሮ መስራት ይገባል ብለዋል።

የትምህርትና የጤና ተቋማትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት የአደንዛዥ እጽ ስርጭትን መከላከል ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የአደገኛ መድሃኒቶችና ትንባሆ ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ባህሩ ዘውዴ፤ ባለስልጣኑ ጥብቅ ቁጥጥር በሚያደርግባቸው የትንባሆና አደገኛ መድሃኒቶች ስርጭት እየተባባሰ ስለመምጣቱ የሚያሳዩ ምልክቶች እንዳሉ አንስተዋል።

ባለስልጣኑ ቀደም ሲል ሲሰራጭ የነበረውን 'ትራማዶል' የተሰኘው ለሱስ የሚዳርግ መድሃኒት በሀኪም ትዕዛዝ ብቻ እንዲሰጥ በማድረግ፣ ስርጭቱን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዳሉት የከተሜነት መስፋፋትና እና መጤ ባህሎችን ተጽዕኖ ተከትሎ የአደንዛዥ እጾች ስርጭት እየተስፋፋ በወጣቶች ስብዕና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያስከተለ ይገኛል።

አደንዛዥ እጾች ወጣቶች ለጤና ችግር እንዲሁም ለኢ-ሞራላዊ ድርጊቶችና ለአገር አፍራሽ ተልዕኮዎች እንዲጋለጡ፣ ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች እንዲሸረሸሩ በማድረግ አገርን ለኢኮኖሚያዊ ስብራት የሚዳርግ ነው ብለዋል።

በስነ ምግባር የታነጹ፣ ጤናማና አምራች ዜጎች ለማፍራት በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ መስራት እንደሚገባው ገልጸው፤ ሚኒስቴሩ ስትራቴጂ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የፀረ-አደንዛዥ እጾች አገር አቀፍ ንቅናቄውም ለተጀመሩ ስራዎች ስኬት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የፀረ-አደንዛዥ እጾች የንቅናቄ  የግንዛቤ ፈጠራ፣ የመከላከልና መቆጣጠር፣ የስነ ልቦና ሕክምና፣ የሕጎችን ተፈጻሚነት ማሳደግ፣ የስብዕና ክበባትን ማስፋፋት፣ የክሊኒካልና ተሃድሶ አገልግሎት፣ የጥናትና ምርምር ስራዎች ማከናወን እንደሚያካትት ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም