በ"ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ" እየታየ የሚገኘው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
በ"ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ" እየታየ የሚገኘው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- ቋሚ ኮሚቴው
ድሬደዋ ፤ ሚያዝያ 4 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- በ"ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ" እየታየ የሚገኘው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤት ይበልጥ የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሶማሌ ክልልና በድሬዳዋ አስተዳደር በኢንዱስትሪና በማዕድን ልማቶች እየተከናወኑ የሚገኙ እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል ።
አባላቱ በድሬዳዋ የኢንዱስትሪ መንደር የመኪና መገጣጠሚያ ፣የኦክስጅን ማምረቻ ፣የብረታ ብረት ፣ የመኪና ባትሪ እንዲሁም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዳግም ወደ ማምረት የተመለሱ ፋብሪካዎች የስራ እንቅስቃሴ ቃኝተዋል።
የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ስራ የጀመሩትን የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን የስራ እንቅስቃሴዎች ተመልከተዋል።
በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኢንዱስትሪው ዘርፍ በሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ ዛሬ ከድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ንዑስ ሰብሳቢ አቶ ዳውድ መሐመድ እንዳሉት ፤ በድሬዳዋ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት አበረታችና ተስፋ ሰጪ ናቸው።
የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና በማዳን፣ ተተኪ ምርቶችን በማምረት፣ የስራ ዕድል በመፍጠር ጥሩ ጅምሮች መኖራቸውን ከጉብኝታቸው መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
በተለይ አገር አቀፍ ደረጃ ለአንድ ዓመት በዘለቀው "የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በድሬዳዋ ተዘግተው የነበሩ አምስት አምራች ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ስራ መግባታቸው የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።
ሆኖም ኢንዱስትሪዎቹ በሙሉ አቅማቸው በማምረት የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡ ያሉባቸውን የግብአትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በተቀናጀ መንገድ መፍታትን በትኩረት መስራት እንደሚገባም ነው አቶ ዳውድ ያሳሰቡት።
የኢንዱስትሪ ዘርፉ ከሚመሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከአስተዳደሩ ጋር በመሆን ቋሚ ኮሚቴው የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ፣ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር፤ አስተዳደሩና የፌደራል መንግስት በቅንጅት እያከናወኗቸው ያሉ የኢንዱስትሪ ስራዎች በዘርፉ ላይ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸዋል።
በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት የተጀመረው የኢንዱስትሪ ንቅናቄ ይበልጥ ለማሳደግና ዘርፉ ያሉባትን ችግር ለማቃለል አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው ጋር ተቀናጅቶ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።