ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ውጤታማ የኢኮኖሚና የፖለቲካ የዲፕሎማሲ ተግባራትን እያከናወነች ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 

አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2015(ኢዜአ) ፡-ኢትዮጵያ ውጤታማ የኢኮኖሚና የፖለቲካ የዲፕሎማሲ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሳምንቱ የተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን  አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በተያዘው ሳምንት መጨረሻ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚኖራቸው ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ በጉብኝታቸው ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እንደሚያደርጉ በመጠቆም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጣሊያን በነበራቸው ቆይታ የኢትዮ-ጣሊያንን የቆየ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገው እንደተመለሱ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ከሁለትዮሽ ጉዳዮች በተጨማሪ በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ የሚገኙ  ወዳጅ አገራት እንደሆኑም ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ጉብኝትም የአገራቱን ወዳጅነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አምባሳደር መለስ አክለውም ኢትዮጵያ በመልሶ ግንባታ እና ሰብዓዊ አቅርቦት ላይ የምታደርገውን ጥረት የጣሊያን መንግስት እገዛ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

በሳምንቱ በድህረ-ግጭት የዲፕሎማሲ ስራ ወዳጅን የማብዛት፣ የማለዘብ እና የማስገንዘብ ውጤታማ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የዲፕሎማሲ ግብ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማስገኘት መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ እያካሄደች የምትገኘው የመልሶ ግንባታ፣ ማቋቋም እና ሰብዓዊ ድጋፍ እገዛን የሚያስገኝ የዲፕሎማሲ ተግባር ነው ብለዋል።

የስሎቬኒያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታንጃ ፋጆን በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በጉብኝታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ስሎቬኒያ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ለመክፈት መወሰኗን አንስተው፤ ውሳኔዋም አዲስ አበባ የአፍሪካ ፖለቲካ ማዕከል መሆኗን እንደሚያፀና ጠቁመው፤ አገሪቱ ከአፍሪካ ሕብረት እና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።

ስሎቬኒያ በግብርና፣ በውሃ ዲፕሎማሲ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በንብ ማነብ ጭምር  ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው በዛሬው ዕለት መሰረቱን እንግሊዝ ያደረገው "ዓለም አቀፍ የጥቁር ህዝቦች ታሪክ ቅርስ እና ትምህርት" ልዑክ ኢትዮጵያ መግባቱንም አስታውቀዋል።

ተቋሙ ዋና መቀመጫውን ኢትዮጵያ በማድረግ አዲስ አበባን የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ማዕከል የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

የልዑኩ ጉብኝት እና የውሳኔው መነሻ ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ጥቁር ህዝቦች ነፃነት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ከግምት እንደሆነ አንስተው፤ ልዑኩ ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚነስትር የስራ ጉብኝትን አስመልክቶ በቀጣይ መረጃ እንደሚሰጥ አንስተው፤ በሚቀጥሉት ሳምንታትም የሌሎች አገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ከመቀዛቀዝ ወጥቶ ወደ ተሻለ ምዕራፍ መግባቱን የገለጹት ቃል አቀባዩ ይህንም ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት መድረክ እንደሚካሄድ በመጠቆም፤ በአሜሪካና ሌሎች ሀገራትም በቀጣይ ቀናት የቢዝነስ ፎረሞች እንደሚከናወኑ አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም