ቀጥታ፡

በቀጣይ አስር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች በተመሳሳይ ዝናባማ ሆነው ይቀጥላሉ- የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2015 (ኢዜአ):-በሚያዚያ ወር ቀጣይ አስር ቀናት  የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች  በተመሳሳይ ዝናባማ ሆነው እንደሚቀጥሉ  የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት  አስታወቀ ።

ኢንስቲትዩቱ በበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተጠባቂ የአየር ሁኔታ አዝማሚያን በሚመለከት ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ በመደበኛ ሁኔታ በመጪዎቹ አስር ቀናት የዝናቡ መጠንና ስርጭት በተሻለ መልኩ እንደሚቀጥል ጠቁሟል።

ለዝናብ መኖር አመቺ የሆኑ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በተለይም በበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ በተመሳሳይ ቀጣይነት እንደሚኖራቸው ትንበያው ያሳያል።

በዚህም በደቡብ፣ በደቡብ ምስራቅ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በምስራቅና በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የዝናብ ሁኔታው የተሻለ እንደሚሆን ይጠበቃል ነው ያለው።

በተለይም የደቡብና የደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ዝናብ እንደሚያገኙ በማመላከት።

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአሮሚያ ክልል ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ቡኖ በደሌ፣ የሸዋ ዞኖች፣ የምዕራብና የምስራቅ ሐረርጌ፣ ሁሉም የአርሲ፣ የባሌና የጉጂ ዞኖች ዝናባማ እንደሚሆኑም ጠቁሟል።

የአዲስ አበባና  ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ሐረሪ ክልል በተመሳሳይ ዝናባማ እንደሚሆኑ  የአየር ሁኔታ አዝማሚያው ያሳያል ብሏል።

በአማራ ክልል የደቡብና የሰሜን ወሎ ዞኖች፣ ምስራቅ ጎጃም ደቡብ ጎንደርና የዋግኸምራ ዞኖች ፣እንዲሁም በትግራይ ክልል የመካከለኛው የምስራቅና የደቡብ ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት፣ በምስራቅ አማራ፣ በባህርዳር ዙሪያ፣ አማን፣ ቴፒ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ትንበያው ጠቁሟል። 

እንዲሁም፣ በአብዛኛው የሶማሌ ክልል፣ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የሲዳማና ጋምቤላ ክልል ዞኖች ዝናባማ ሆነው እንደሚቆዩ ትንበያው ያመለክታል።

በመጪዎቹ አስር ቀናት በሚኖረው ዝናባማ የአየር ሁኔታ የበልግም ሆነ አንዳንድ የመኸር ሰብል አብቃይ የሆኑ አካባቢዎች አንጻራዊ በሆነ መልኩ ከፍተኛ እርጥበት እንደሚያገኙም ተገልጿል።

ይህም አስቀድመው ለተዘሩና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎችም ሆነ ለቋሚ ተክሎች፣ ለአርብቶ አደሮች ግጦሽና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጠቀሜታው የጎላ ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል በዚህ ወቅት አልፎ አልፎ የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ በማሳዎች ላይ የውሃ መተኛትና የአፈር መሸርሸር ሊያስከትል ስለሚችል ተገቢው ጥንቃቄ እንዲወሰድ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

በአብዛኛው ሰምጥ ሸለቆ፣ ኦሞ-ጊቤ፣ ገናሌ-ዳዋ፣ የላይኛውና የመካከለኛው አባይ፣ አዋሽ፣ ባሮ አኮቦ፣ ዋቢሸበሌ እና የላይኛው ተከዜ እንዲሁም አፋር ደናክል ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ ዝናብ እንደሚጠበቅ በመጠቆም።

በተለይም ተዳፋታማ በሆኑ አካባቢዎች በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

በሌላ በኩል ጥቂት የሀገሪቱ አካባቢዎች በአመዛኙ ደረቃማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖራቸው በትንበያው ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም