በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል - የግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል - የግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2015(ኢዜአ) በዘንድሮው የክረምት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የበጋ ወቅት በተቀናጀ የኅብረተሰብ ተፋሰስ ልማት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር የአፈርና የውኃ ጥበቃ ሥራ ተከናውኗልም ተብሏል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ እና የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም በበጋ ወቅት የተፋሰስ ሥራዎች አፈፃፀምና በቀጣይ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ስራዎች ዙሪያ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ላለፉት አራት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በስኬት አከናውናለች፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ መዛባት በተከሰተ ድርቅና ጎርፍ በዜጎች ላይ የሚደረሰውን ጉዳት ለመከላከል ከአፈርና ውሃ ጥብቃ ባለፈ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዘላቂነት ለመቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የተገኘውን ስኬት ለማስቀጠል በዘንድሮው የክረምት ወቅት 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም በበኩላቸው፤ በአረንጓዴ አሻራ የተመዘገበው እመርታ መንግስት ያቀደውን መፈጸም እንደሚችል ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለዘንድሮው መርሀ ግብርም 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኞች ለተከላ የተዘጋጁ ሲሆን፤ አጠቃላይ ከሚተከለው ችግኝ 45 በመቶ የሚሆነው ለደን ዛፍ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡
ለተከላ ከተዘጋጀው ችግኝ 55 በመቶ የሚሆነው ለጥምር ግብርና፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም ለእንስሳት መኖ የሚያገለግል መሆኑንም እንዲሁ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመትከል ከታቀደው ችግኝ ውስጥ 80 በመቶውን የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንደሚተክሉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ በአፈር መሸርሸርና ጎርፍ ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከል ከአረንጓዴ አሻራ በተጨማሪ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በዘንድሮው ዓመት ኅብረተሰቡ በባለቤትነት በሚመራው የበጋ ወቅት የተቀናጀ የኅብረተሰብ ተፋሰስ ልማት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ እስካሁን ባለው መረጃ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር ተከናውኗል ብለዋል።
ከጥር ወር ጀምሮ በተከናወነው የተፋሰስ ልማት ኅብረተሰቡ በፍላጎቱ በዓመት 30 ቀን የነፃ አገልግሎት በመስጠት ላደረገው አስተዋፅኦ ላቅ ያለ ምስጋና እንደሚገባ ተናግረዋል።
የተፋሰስ ሥራ ጥበቃው ቀጣይነት እንዲኖረው ከ2 ሺህ 240 በላይ ማኅበራት በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተው የተፋሰሱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።