የጸረ አደንዛዥ ዕፆች ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የጸረ አደንዛዥ ዕፆች ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ተጀመረ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2015(ኢዜአ):-የጸረ አደንዛዥ ዕፆች ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ተጀመረ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የፀረ አደንዛዥ ዕፆች ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በይፋ አስጀምሯል።
በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ተገኝተዋል።
አደንዛዥ ዕፅ በወጣቱ ትውልድ ላይ ከስነ ምግባር ግድፈት እስከ የስነ ልቦና ቀውስ ድረስ ችግር በመፍጠር አምራቹን ሀይል እየጎዳ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በተለይ ወጣቱን ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች፣ ለወንጀል ፣ ድብርትና መሰል ተፅዕኖዎች የሚዳርግም ነው።
የንቅናቄ መድረኩ ከተያዘው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ለቀጣይ አንድ ዓመት የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዳሉት በሀገሪቱ ከፍተኛ ድርሻ ባላቸው ወጣቶችና ታዳጊዎች ላይ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰ በሀገር ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ መረጋገጥ ወሳኝ ሚናቸውን እንዲወጡ ማድረግ ይገባል።
ወጣቶች እምቅ አቅምና የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ትኩስ ኃይል በመሆናቸውና ለሀገር ዕድገት አበርክቷቸው ከፍተኛ በመሆኑ፤ ለአደንዛዥ ዕፆች እንዳይጋለጡ ሁለንተናዊ ስብዕና መቅረፅ፣ በዕውቀትና ክህሎት እንዲዳብሩ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም የከተሜነት መስፋፋትና መጤ ባህሎች አደንዛዥ ዕፆች እንዲስፋፉ የማይናቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በወጣቶች ስብዕና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል።
አደንዛዥ ዕፆች ወጣቶች ለኢ-ሞራላዊ ድርጊቶችና ለሀገር አፍራሽ ተልእኮዎች መሳሪያ እንዲሆኑ እያደረገ በመሆኑ የጋራ ርብርብና ስራ ይፈልጋል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ አደንዛዥ ዕፆች ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች በግለኝነት አስተሳስብ እንዲሸረሸሩ ያደርጋሉ።
በወጣቶችና ታዳጊዎች ጤና ላይ ጉዳት በማድረስም ኢኮኖሚያዊ ስብራት እያስከተሉ በመሆኑ ችግሩን ከወዲህ መግታት ይገባል ነው ያሉት።
ወጣቶች በስነ ምግባር የታነፁ፣ ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ ሊሰራ ይገባል።
ለዚህም በሚኒስቴሩ ስትራቴጂ ዕቅድ ተዘጋጅቶ የወጣቶችና ታዳጊዎችን ሰብዕና ለመገንባትና የፀረ አደንዛዥ ዕፆች ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን ወደ ስራ ተገብቷል ነው ያሉት።
የሱስ ማገገሚያ ማዕከላትን በማጠናከር፣ የአደንዛዥ ዕፆችን ዝውውር በመግታት ከምንም በላይ ደግሞ በወጣቶች ስብዕና እና ስነ ምግባር ግንባታ ላይ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የፀረ አደንዛዥ ዕፆች ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ለተጀመሩ ስራዎች ስኬት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።