ቀጥታ፡

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2015(ኢዜአ):- የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከሚያዝያ 6 እስከ 7 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ ከኢፌዴሪ መንግሥት እና ከአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሏል።

የሚኒስትሯ ጉብኝት ዋነኛው አጀንዳ ጣሊያን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሰብዓዊ እና የልማት ድጋፍ ማጠናከር እንደሚሆን ተጠቁሟል።

ጣሊያን የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ ይታወቃል።

ጉብኝቱ የኢትዮጵያ እና የጣሊያንን አጋርነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በሚጋሯቸው ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም