በድሬደዋ ከተማ የኖራ፣ የሲሚንቶና የብረት ፋብሪካዎችን ያካተተ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ ከተማ የኖራ፣ የሲሚንቶና የብረት ፋብሪካዎችን ያካተተ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሊገነባ ነው
አዲስ አበባ ሚያዚያ 3 /2015 (ኢዜአ)፦ በድሬደዋ ከተማ የኖራ፣ የሲሚንቶና የብረት ፋብሪካዎችን ያካተተ የመልካ ጀብዱ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሊገነባ ነው።
ግንባታውን የሚያከናውነው የቻይናው ዓለም አቀፍ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሲኖማ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ነው።
ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ ከቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ጋር በጥምረት የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካን የሚገነባ አገር በቀል ኩባንያ ነው።
በዛሬው ዕለትም በ106 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባውን የመልካ ጀብዱ ኢንዱስትሪል ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ለማስጀመር የናሽናል ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ከሲኖማ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ጋር ሥምምነት ተፈራርመዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቲዎስ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት በድሬደዋ ከተማ የሚገነባው ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካ ለምስራቅ አፍሪካ አገራት ገበያ ምርት የሚያቀርብ ነው።
ግንባታው ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በዓመት ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘት የሚያስችል ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ ሊቀ-መንበር አቶ ብዙአየሁ ታደለ ግንባታው 540 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚወስድ ሲሆን ዛሬ የሚፈረመው የመጀመሪያ ዙር ግንባታ 243 ሚሊየን ዶላር ወጭ ይደረግበታል ብለዋል።
ፖርኩ ሲጠናቀቅ በዓመት 700 ሺ ቶን የማምረት አቅም ያለው የብረት ፋብሪካ፣ በቀን አንድ ሺ ቶን የማምረት አቅም ያለው የኖራ ፋብሪካ፣ በዓመት ሦስት ሚሊየን ቶን ማምረት የሚችል ሲሚንቶ ፋብሪካ መሆኑን ገልጸዋል።
የሲኖማ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ተወካይ ሊን ጆንግ ፕሮጀክቱን በፍጥነትና በጥራት አጠናቀን በማስረከብ የኢትዮጵያ ህዝብ የጣለብንን እምነት እንወጣለን ብለዋል።