ዩኒሴፍ ድርቅ እና ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ህፃናት ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒሴፍ ድርቅ እና ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ህፃናት ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2015(ኢዜአ)፦ ዩኒሴፍ ድርቅ እና ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ህፃናት ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ ተወካይ ዶክተር አቡበከር ካምፓ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ እንዳሉት ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ልማት ላይ ቁልፍ ድጋፍ እያደረገ ያለ አጋር መሆኑን በመጥቀስ ይበልጥ በህፃናት የተመጣጠነ ምግብ እና ትምህርት እንዲዳረስ እየተገበራቸው ያሉ መርሀ ግብሮችን አድንቀዋል።
ዩኒሴፍ ድርቅ እና ግጭት በነበሩባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ህፃናት ትኩረት መስጠት እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አመልክተዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች ለሚገኙ ህፃናት የሚያደርጋቸውን የሰብአዊ ድጋፎች እና የልማት ስራዎች ይበልጥ እንዲያጠናክር አቶ ደመቀ ጠይቀዋል።
በኘሪቶሪያ ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት አተገባበር አቶ ደመቀ ለተወካዩ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን መንግስት በሙሉ ቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ዶክተር አቡበከር ካምፓ በበኩላቸው በኘሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ እና ድጋፍ ለሚሹ ህፃናት የሰብአዊ እርዳታን ተደራሽ ለማድረግ የተሻለ ሁኔታ መፍጠሩን ተወካዩ ገልፀዋል።
ዩኒሴፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር አቡበከር ካምፓ አስታውቀዋል።
ዩኒሴፍ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚያከናውናቸው የልማት እና የተራድኦ ስራዎች ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ የተናገሩት ዶክተር አቡበከር ዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ሁነኛ የልማት አጋር ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።