ቀጥታ፡

ናሽናል ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ በኢትዮጵያ የሚታየውን የግንባታ እቃዎች እጥረት ይፈታል--የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 03/2015(ኢዜአ)፦ ናሽናል ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ በኢትዮጵያ የሚታየውን የግንባታ እቃዎች እጥረት መፍታት የሚችል መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

የናሽናል ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲግ በድሬዳዋ በሚያስገነባው የመልካ ጀብዱ የሲሚንቶ፣ ብረትና ኖራ ፋብሪካ ግንባታ ስምምነት ላይ ተገኝተው በሰጡት መመሪያ፣ ኩባንያው ከፍተኛ የፕሮጀክት አስተዳደር ስርዓት ያለው ግዙፍ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

በድሬዳዋ የሚገነባው የሲሚንቶ፣ ብረትና ኖራ ፋብሪካ የወቅቱ ፈተና የሆነውን የግንባታ እቃዎች እጥረት የሚፈታ ይሆናልም ብለዋል።

ሚኒስቴሩ የግንባታ ግብዓቶችን አምራች ኢንዱስትሪዎችን የማበረታታትና የመደገፍ ስልጣን እንደተሰጠው ገልጸው፣ ምርት በብዛት እንዲመረትና ገበያው እንዲዘምን በማድረግ ሀላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።

የናሽናል ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲን የሀገር ውስጥ የምርት ፍጆታን በለሚ ናሽናል በመሸፈን በመልካ ጀብጁ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት የሚችል ነው ብለዋል።

ኩባንያው የስራ እድል ከመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባለፈ የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ የሚያስተዋውቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም