የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶችን ጥራት በማረጋገጥና ግብይቱን በማዘመን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶችን ጥራት በማረጋገጥና ግብይቱን በማዘመን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ እየተሰራ ነው
ሐዋሳ ሚያዚያ 03 /2015 (ኢዜአ) የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶችን ጥራት በማረጋገጥና ግብይቱን በማዘመን የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ በግብርናው ዘርፍ እየተከናወነ ያለው የለውጥ ስራ አበረታች ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በሀገሪቱ አራተኛ የሆነውን የሃዋሳ ምርት ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን ማእከል ዛሬ አስመርቋል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ፍትሃዊ፣ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የግብይት ስርዓት በመገንባት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
ጥራት ያለውን ቡና ለአለም ገበያ በማቅረብ ተገቢውን ዋጋ ለማግኘት የሚደረገውን ሂደት በዘመናዊ የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬሽን ቁጥጥር ስርዓት ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በዚህም እንደ ሃገር አራተኛ የሆነው የሃዋሳ የምርት ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን ማእከል አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ማእከሉ አርሶአደሩን፣ አቅራቢውንና የባለሃብቱን ጊዜ በመቀነስ ጥራት ያለው ቡና ለአለም ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ከቀጥታ ግብይት ስርዓት ጋር የተያያዘ የቡና ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን አገልግሎት ስራው ከሚዛን አገልግሎት ክፍያ መዘግየትና ከገንዘብ እጥረት ጋር ይነሳበት የነበረውን ችግር እንደሚፈታ ጠቁመዋል።
በአካባቢው የቡና ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት በዘርፉ የሚፈጠረውን ሰፊ የስራ እድል እንደሚያሳድግም ገልጸዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ በበኩላቸው ለበርካታ ዓመታት የሃገሪቱን ኢኮኖሚ እየመራ ያለውን የግብርና ዘርፍ ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት አበረታች ለውጥ እያሳዩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ግብርናው ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የሚደረገውን መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት ተልእኮውን እንዲወጣ የተጀመሩ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በዘርፍ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት የቡና ዘርፍ በዘመናዊ አሰራር ማገዝና አገልግሎቱን ለባለሀብቱና በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ እንደገለጹት፤ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ አበባ እና መሰል የግብርና ምርቶች 80 በመቶ የሃገሪቱን የውጭ ንግድ ይሸፍናሉ።
ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ በተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት ግብርና ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዝ አስታውሰው፤ በቅርቡ በበጋ መስኖ ስንዴ የተጀመረው ስራ በሃገሪቱ አዲስ ምእራፍ የከፈተ ነው ብለዋል፡፡
የቡና ዘርፍ ባሉበት በርካታ የተወሳሰቡ ምክንያቶች ለኢኮኖሚው ማበርከት ያለበትን ያህል ሳያበርክት ቢቆይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተሰራው ስራ ከፍተኛ ውጤት እየመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቡና ምርት ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን ማእከላት መስፋፋት የተገኘውን ውጤት ይበልጥ እንደሚያሳድግም ተናግረዋል።
የቡና ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽ ማእከላት በማስፋፋት ወደ አምራቹ ማድረስ በግብርናው ዘርፍ የተጀመረ የለውጥ ስራ ማሳያ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ናቸው፡፡
የማእከሉ መከፈት የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት በማሳደግና የቡና ግብይቱን በማዘመን በዘርፉ የሚገኘውን ውጤት ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል፡፡
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው ቡና በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ዘርፍም የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ በርካታ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡
ዘርፉን የሚያዘመኑ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ የአርሶአደሩን፣ የአምራቹንና የአቅራቢውን ትስስር በማሳለጥ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከ451 በላይ የቡና ላኪ ኢንዱስትሪዎችና ከ200 በላይ ቡና ላኪ አርሶአደሮች መኖራቸውን ገልጸው፤ የማእከሉ መከፈት የክልሉን የቡና ልማት ስራ ያሳድገዋል ብለዋል፡፡
በመድረኩ ለማእከሉ መከፈት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትና ለቡና አምራች አርሶአደሮች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።