በአዲስ አበባ ተቋማት ለዜጎች የሚሰጡትን አገልግሎት አሰጣጥ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ለማሻሻል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ተቋማት ለዜጎች የሚሰጡትን አገልግሎት አሰጣጥ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ለማሻሻል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል
አዲስ አበባ ሚያዚያ 3/2015/ኢዜአ/ ፡-በመዲናዋ ተቋማት ለዜጎች የሚሰጡትን አገልግሎት አሰጣጥ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ለማሻሻል ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው በኢኮኖሚ ዘርፍ ከተመረጡ ተቋማት ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ተወያይቷል።
በውይይቱም የሕዝብ ክንፍ ተወካዮች፣ ሸማች ማኅበራት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሄ ሃሳቦች ላይ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱም ላይ ተቋማቱ እየሰጡ ባለው አገልግሎት፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የተቋማቱ ኃላፊዎች የውይይት መነሻ ጹሁፍም አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሂክማ ከይረዲን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ቢሮው ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት የዜጎችን እርካታ ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ድጋፍ እያደረገ ነው።
በተቋማት በኩል አዳዲስ አሰራሮች እንዲዘረጉ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር ሰፋፊ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
ለአብነትም እንደ ገቢዎችና ንግድ ቢሮ ዓይነት ተቋማት ዜጎች ካሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ የዜጎችን ፍላጎት ከማርካት አኳያ ሙሉ በመሉ ችግሮች ተቀርፈዋል ማለት አይቻልም ያሉት ሃላፊዋ ችግሮችን በጥናት ላይ ተመስርቶ የመፍታት ጉዳይ ትኩረት ተደርጎበት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ብልሹ አሰራሮችን እንዴት መከላከል ይቻላል?፣ አገልግሎት አሰጣጡን በምን መልኩ ውጤታማ ማድረግ ይቻላል? በሚለው ዙሪያ በጥናት የተደገፈ ማሻሻያ ለማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ በበኩላቸው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ እንዲሁም የዜጎችን ጉልበትና ጊዜ ለመቆጠብ ቢሮው ዘመናዊ አሰራሮችን እየዘረጋ ነው።
ግብር ከፋዮች በቴክኖሎጂ በመጠቀም ግብር እንዲከፍሉ የተጀመረው ሥራ በጎ ውጤቶች እየተገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ ከተሳተፉት ተገልጋዮች መካከል አቶ ጌታቸው ኮሩ፤ ሴክተር ተቋማት የሚሰሩት ሥራ መሬት መውረዱን የማረጋገጡ ሥራ አጽንዖት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ሻለቃ በዳሳ ቱጂ በበኩላቸው በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ያለው የሰው ኃይል ብቁ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም የአገልግሎት ሰጪነት አመለካከት ማጎልበት እንዳለበትም በማንሳት።