ቀጥታ፡

በዘመን ሂደት የላሉና የተሸረሸሩ ማኅበራዊ እሴቶችን ትንሳኤ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2015(ኢዜአ) በዘመን ሂደት የላሉና የተሸረሸሩ ማኅበራዊ እሴቶችን ትንሳኤ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ 'የሀሳብ መዋጮ፤ የእሴቶቻችን ትንሳኤ' በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የመጀመሪያ የወግ መድረክ የተለያዩ ሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በታደሙበት ተካሂዷል።


 

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሒሩት ካሳው፤ ነባር ባህላዊ እሴቶች ለኢትዮጵያ መጽናት ካስማ ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ካስማዎች ኢትዮጵያ ከገባችበት አሁናዊ ችግር እንድትወጣ ጉልህ ሚና ስላላቸው ለእሴቶች የትንሳኤ ሃሳብ ማዋጣት እና ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በዚህም ቢሮው በተከታታይ የሚደረግ 'የሃሳብ መዋጮ' በሚል የወግ መድረክ ማዘጋጀቱን ገልጸው፤ ሃሳብ ያለው ባለድርሻ አካል ሁሉ በቀጣይ ወጎች እየታደመ ለሀገር ግንባታ የሚበጅ ሃሳቡን እንዲያጋራ ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ-ጽሑፍ መምህርና ተመራማሪው ዶክተር መሀመድ አሊ፤ 'የባህል እሴቶች በፎክሎር ዕይታ' በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ "እሴት"ን የሰናይ እና እኩይ ባህሪያትን የሚለይ ልባዊ፣ አካላዊና አዕምሯዊ ክዋኔ በሚል በይነውታል።

በሁሉም ማኅበራዊ፣ ስነ-ልቦናዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እሴቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ሰብዓዊነት ማስረፅን፣ ከዳኝነት በፊት ፍትሕን፣ ከዕውቀት በፊት እዝነትን፣ ከሙያ በፊት ሰብዓዊነት እና ግብረገብነትን የማስተማር ፋይዳ እንዳላቸው አንስተዋል።


 

ከእሴቶች ማሰራጫና ማጎልበቻ መንገዶች መካከል ተረቶች፣ ምሳሌያዊ ንግግሮች፣ ምርቃትና እርግማን፣ አከባበርና ሥርዓቶች እንዳሉ ጠቁመው፤ እነዚህ እሴቶች በጊዜ ሂደትና በሥርዓተ-ትምህርት እየተሸረሸሩ ስለመምጣታቸውም ተናግረዋል።

በዚህም ሚዲያዎች፣ ሥርዓተ-ትምህርቱና የአስተዳደር ሥርዓቱ እሴቶችን የተላበሰና ዕውቅና የሚቸሩ እንዲሆኑ በጥንቃቄ መስራት እንደሚገባ ነው የገለጹት።

የፍልስፍና መምህሩ ኢያሱ ባሬንቱ፤ 'እሴቶች ከፍልስፍና አንፃር' በሚል ባቀረቡት መነሻ ጽሑፍ ደግሞ፤ የሰው ልጅ ህሊናን የመግራት፤ ዓለማትን የማወቅና የመረዳት ሸክሞች እንዳሉበት ጠቅሰው፤ በሰው ዑደተ- ሕይወት አንዱ ከሌላው ሰው እንዲሁም ከልዕለ-ተፈጥሮ ጋር ባለው መስተጋብር የራሱን እሴቶች ያጎለብታል። 

በዚህ ዑደተ-ሕይወት ኢትዮጵያዊያንም ዓለምን የሚረዱበት እና ከሰውነት ማንነታቸው የመነጩ እሴቶችን ገንብተው ከትውልድ ትውልድ እንዳሻገሩ በመጥቀስ፤ በዘመን እና በትውልድ ወንዝ መለዋወጥ የተሸረሸሩ እሴቶችን መፈለግ ያሻል ብለዋል።


 

በታሪክ ሂደት የትውልድ ወንዝን ተሻግሮ ለመናበብ፣ ሀገራዊ ውል ለማፅናት ወንድማማችነትና እህትማማችነትን እንዲሁም ማኅበራዊ ጥሪትን ማጎልበት፣ ዛሬና የትናንት አተያይ መነጽርን ማስተካከል፣ ትምህርትና ተግባቦትን መፈተሽ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያዊያን በባህልና በአኗኗር ዘይቤ ለዘመናት አብሮነታቸው የጋራ እሴቶች ቢገነቡም እነዚህ እሴቶች እየላሉና እየተሸረሸሩ አደጋ ውስጥ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ትንሳኤያቸውን ማብሰር የትውልዱ ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ መምህርና ተመራማሪው ዶክተር ዘላለም ተፈራ፤ የማኅበራዊ እሴቶቻችን ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው' በሚል ባቀረቡት መነሻ ጽሑፍ ማኅበራዊነትና ሰብዓዊነት ነባር የሀገሬው እሴት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለኃይማኖት ቀናዒ፣ ምግባረ-ሰናይ፣ ደጋግ ሰዎች እንደሆኑ ከጥንት ፀሐፍትና ፈላስፎች መካከል የግሪክ ፈላስፎችን በምስክርነት ጠቅሰዋል።

በነብዩ መሀመድ የፍትሕ ምድርና ፍትሐዊ ንጉሥ ሀገርነቷ የተመሰከረላት እና የብዝሃነት እሴት ባለቤት እንደሆነችም ጠቅሰዋል።

'ዑደተ-ሕይወት እሴትን፣ እሴት ደግሞ ትውልድን ይቀርፃል' ያሉት ምሑሩ፤ ኢትዮጵያዊያን ጥፋትን የሚገስፅ፣ በጎነትን የሚያሞካሽ፣ አብሮነት እና የጋራ ስነ-ልቦና የሚያዳብር እሴት ያላቸው ህዝቦች ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።


 

በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ ቋንቋዎችና ድርጊቶች ደግነትና መተዛዘን፣ መከባበርና እንግዳ ተቀባይነት፣ ሀገር ወዳድነትና አርበኝነት፣ ማኅበራዊነትና መልካም ጉርብትና፣ ዕውነትን መሻት እሴቶች ዛሬም ተደብቀው እንዳሉ ጠቅሰዋል።

ምሑሩ የእሴቶችን ትንሳኤ ለማብሰር ዘመናዊነትና ከተሜነትን ከሀገር ነባራዊ አውድ ጋር ባጣጣመ መልኩ ሥርዓት መዘርጋት፣ እንዲሁም ሥርዓተ-ትምህርትን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

እሴቶች ከማኅበረሰብ ዕድገት ጋር ቢለዋወጡም ለማኅበራዊ እሴቶች ማስጠበቂያ መንገዶችን መለየት፣ ለነባር ባህላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ነው ያነሱት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም