ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ስሎቬኒያ በኢትዮጵያ ሴቶችን ለማብቃት በትብብር ለመስራት ተስማሙ

 

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ስሎቬኒያ በኢትዮጵያ ሴቶችን ለማብቃት በትብብር ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተስማሙ።

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከስሎቬኒያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታንጃ ፋጆን ከተመራው ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም የኢትዮጵያ መንግስት ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፎች ለማብቃት ቁርጠኛ ስለመሆኑ ዶክተር ኤርጎጌ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያን እና የስሎቬኒያን ትብብር ማሳደግ የሚያስችል ሰፊ አቅም እንዳለ የገለጹት ዶክተር ኤርጎጌ  ይህንን አቅም በመጠቀም ኢትዮጵያ ከስሎቬኒያ ጋር ያላትን ትብብር ማጠናከር ትፈልጋለች ብለዋል።

የስሎቬንያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታንጃ ፈጆን በበኩላቸው ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ በነጻ የትምህርት ዕድል በማመቻቸትና በሴቶች ጥቃት ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ እና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ስሎቬኒያ ከኢትዮጵያ ጋር የመስራት ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

ውይይቱ በተለይ በኢትዮጵያ ሴቶችን በማብቃት ዙርያ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም