በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የዲጂታል ፋይናንስ ምን ይመስላል?

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የዲጂታል ፋይናንስ ምን ይመስላል? ያጋጠሙት ተግዳሮቶች ምንድናቸው? መፍትሄዎቹስ?

በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ አገራዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባትና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተጠቅሷል።

ከእነዚህም ተግባራት መካከል የተቋማትን የኢንተርኔት ትስስር ሽፋንና የመጠቀም ደረጃን በማሻሻል በኦንላይን በቀጥታ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ማሳደግ ትኩረት ያደርጋል። 

በተለይም ደግሞ ሕዝቡ አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክስ አግባብ እንዲያገኙ ትኩረት ይሰጣል ተብሏል።

ይህንንም ተከትሎ መንግሥት በርካታ ተግባራት እያከናወነ ሲሆን ከእነዚህ ተግባራት መካከል የዲጂታል ፋይናንስ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ነው የሚነሳው።

የወረቀት ገንዘብ ልውውጥን በማስቀረት አሁን ላይ እየተነቃቃ የመጣው የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓትን ይበልጥ ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ እሙን ነው።  

ለአብነትም በኢትዮጵያ የሚገኙ ባንኮች የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ በመጠቀም ደንበኞቻቸው በርካታ መጠን ያለው ገንዘብ በየቀኑ ዝውውር እየፈጸሙ ይገኛሉ። 

ኢትዮ-ቴሌኮም በቅርቡ ባስጀመረው "ቴሌ ብር" እንኳን ከ30 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማፍራት ተችሏል፤ በዚህም በቢሊየን ደረጃ ገንዘብ እየተንቀሳቀሰ ነው። 

አሁን ላይ የዲጂታል ፋይናንስ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ቁጥር እያደገ የመጣ ሲሆን በርካታ ተቋማትም የክፍያ ሥርዓታቸውን በሞባይል ባንኪንግ ሥርዓት በማዞር ላይ ይገኛሉ።  

በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ትግበራ አሁን ላይ ያለበት ደረጃ፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና መፍትሔዎቹን አስመልክቶ ኢዜአ የኢኮኖሚ ምሑሩን አቶ ክቡር ገናን አናግሯቸዋል። 

አቶ ክቡር ገና እንደገለጹት፤ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ቁልፍ ጉዳይ የሆነው የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓትን ማዘመን አገራት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩበት ያለ ዋንኛ ጉዳይ ነው።

የዲጂታል ፋይናንስ በተለይም የባንክ አገልግሎቶችን በቀላሉ ለሕዝቡ ተደራሽ በማድረግ ተገልጋዩን ያለ እንግልትና በቀላሉ ጉዳያቸውን ለመፈጸም እንደሚያስችል ተናግረዋል። 

ይህ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት የገንዘብ ዝውውርን ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ጥሬ ገንዘብ ወደ ዲጂታል ለመቀየር ያለመ አዲስ የቴክኖሎጂ ሽግግር መሆኑን ጠቁመዋል።  

የዲጂታል ፋይናንስ መንግሥት ዘርፉን ለማነቃቃት በአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱ ትኩረት መሰጠቱ፣ እንዲሁም የማስፈጸሚያ መመሪያና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል። 

የዲጂታል ፋይናንስ በኢትዮጵያ አሁን ላይ በጅምር ያለ መሆኑን በተለይም የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማቶችን ይበልጥ በማስፋት ሥርዓቱን ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል።  

በዚህም ላይ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጋራ በመሆን ጥናት ላይ የተመሰረተ አቅጣጫ በማስቀመጥ የዲጂታል ፋይናንስ የሚሰፋበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።   

በተለይም የኢንተርኔት መሰረተ-ልማቶች ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመንና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ የሚያስችል የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራትም ሌላው ትኩረት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። 

በቅርቡ የቴሌኮምና የባንክ ዘርፉ ለግሉ ለውጭ ባለኃብቶች ክፍት መደረጉ ለዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱ መጠናከር አበረታች እርምጃ መሆኑንም አንስተዋል።

በተለይም ደግሞ ከዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የሚነሱ የማጭበርበርና ሌሎች ሕገ-ወጥ ተግባራትን መከላከል የሚያስችል ጠንካራ አሠራሮችን ይበልጥ ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። 

ሕዝቡም አሁን በተዘረጋው የዲጂታል የገንዘብ ልውውጥ ይበልጥ ተሳታፊ በመሆን አገሪቱ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የምታደርገውን ሽግግር እውን ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል። 

የግሉ ዘርፍ ተቋማትም የዲጂታል ፋይናንስ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋልና መጠቀም እንደሚገባ ምክረ-ሃሳብ ሰጥተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም