በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት እየተደረገ ነው- የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት እየተደረገ ነው- የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ ሚያዝያ 03/2015(ኢዜአ)፦ በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ገለጸ።
እ.አ.አ በ2020 በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያ በአንድ አትሌት ተወክላ አበረታች ውጤት አስመዝግቧል።
በወቅቱ በውድድሩ ላይ የተሳተፈው አትሌት ሰለሞን ቱፋ ሰባተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማ ማምጣት ችሏል።
በቀጣይ እ.አ.አ በ2024 በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያስችላት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍቅሩ ተቋም፤ ፌደሬሽኑ ለኦሊምፒክ ውድድሩ ብሔራዊ ቡድን የሚመረጥበት የግል የበላይነት ሻምፒዮና በመጋቢት ወር 2015 ማካሄዱን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ለሁሉም ተሳትፎ ክፍት በተደረገው የግል የበላይነት ሻምፒዮና ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ስፖርተኞች በስልጠና ሂደት በየጊዜው አቅማቸው እየታየ የሚቀነሱ ስፖርተኞች እንደሚኖሩ ተናግረዋል።
የቡድኑ ስፖርተኞች ምርጫ የተካሄደው በአዋቂዎችና ወጣት ምድብ መሆኑን አመልክተዋል።
በአዋቂና ወጣት በሁለቱም ምድብ የተመረጡት ስፖርተኞች አገራቸውን ወክለው በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድር ይሳተፋሉ።
በተለይ በአዋቂ ምድብ የተመረጡት ለኦሊምፒኩ ጨዋታ እጩ ከመሆናቸው በተጨማሪ በሌሎች አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የአዋቂዎች ወርልድ ቴኳንዶ ውድድሮች ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ገልጿል።
እ.አ.አ በ2024 በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ከተለያዩ አገሮች 128 ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ ከዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።
የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት በኦሊምፒክ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካተተው እ.አ.አ በ2000 በሲዲኒ በተካሄደው 27ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ሲሆን በወቅቱ 103 ስፖርተኞች ተሳትፎ አድርገዋል።