የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በቀጣይ ዓመት ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉትን ዝግጅቶች ማጠናቀቁን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በቀጣይ ዓመት ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉትን ዝግጅቶች ማጠናቀቁን አስታወቀ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 03/2015 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በቀጣይ አመት ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉት ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና አስታወቁ።
የዩኒቨርስቲዎች “ራስ ገዝ” መሆን፤ የአካዳሚ፣ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የሰው ሀብት አስተዳደራቸው ላይ ነጻነት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ በትምህርት ሚኒስቴር መገለጹ ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ አመት ራስ ገዝ ለመሆን ሲያደርግ የነበረውን ዝግጅት በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ፕሬዘዳንቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲመሰረት ራስ-ገዝ እንደነበር አስታውሰው፤ በተለያዩ ምክንያቶች ራስ-ገዝነቱን አጥቶ መቆየቱን ገልጸዋል።
ከረዥም ዓመታት በኋላ እንደገና ራስ-ገዝነቱን እውን ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ፕሮፌሰር ጣሰው ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲዎችን የኢኮኖሚና አስተዳደራዊ ነፃነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በመሆኑም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ-ገዝ ለመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቶ ማጠናቀቁን ፕሬዝዳንቱ ይፋ አድርገዋል።
የፋይናንስና የሰው ኃይል አደረጃጀት መመሪያ ተዘጋጀቶ ከሠራተኞች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፤ መመሪያው በቀጣይ ለቦርድ ውሳኔ የሚቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ-ገዝ ለመሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራውን አጠናቆ የአዋጁን መጽደቅ በመጠባበቅ ላይ ይገኛልም ብለዋል።
በ1942 ዓ.ም 33 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ላይ በ14 ካምፓሶች 70 የቅድመ-ምረቃ እና 293 የድህረ-ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞችን እየሰጠ ይገኛል።
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የምርምር ተልዕኮ የተሰጣቸውና የመጀመሪያው ትውልድ ተብለው የተለዩ አሥር ዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝ አስተዳደር እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።