ቀጥታ፡

ምክንያታዊና አገሩን የሚወድ ትውልድ ለመገንባት ትምህርት ቤቶች ከእውቀት ባሻገር ለአገር በቀል እሴቶችና ስብእና ግንባታ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 3/2015(ኢዜአ)፡-ምክንያታዊና አገሩን የሚወድ ትውልድ ለመገንባት ትምህርት ቤቶች ከእውቀት ባሻገር ለአገር በቀል እሴቶችና ስብእና ግንባታ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የአዲስ ወግ “የመደመር ትውልድን መቅረጽ” በሚለው ርዕስ የትምህርት ሚንስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የለባዊ ት/ቤት ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር ፓኖስ ሀዘንድሪያስ፣ የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ በአምላክስራ ፋሲል እና የስነልቦና ባለሙያዋ ሰብለ ሀይሉ በሃሳብ አቅራቢነት፤ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፕሬሽን ሮጋዜጠኛ አልዓዛር ታደለ አወያይነት እየተካሄደ ነው።


 

የውይይት መነሻ ሃሳብ ካቀረቡት መካከል የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ኢትዮጵያ ያሏትን ጸጋዎች በአግባቡ እንድትጠቀም ምክንያታዊና አገሩን የሚወድ ትውልድ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ከቤተሰብ ጅምሮ የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

በአዲሱ የትምህርት ስርዓት ትምህርት ቤቶች ከእውቀት ባሻገር በስብዕና ግንባታ ላይ እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው የመደመር ትውልድ መጽሃፍ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ትውልድ እንዴት እንፍጠር የሚል የዉይይት አውድ እንዲኖር ምቹ እድል መፍጠሩንም  አንስተዋል።

በትምህርት ዘርፍ ላይ የሚሰሩት ፕሮፌሰር ፓኖስ ሀዘንድሪያስ በበኩላቸው የትምህርት ስርዓታችን በአገር በቀል እውቀቶች የተቃኘ ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰቦች ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።


 

ለአመታት ሲተገበር የቆየው የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት የአገር በቀል እሴቶችን ያገለለ እንደነበር አስታዉሰው፤ ይህም ትውልዱ የአገሩን ነባራዊ ሃቅ በሚገባ እንዳይገነዘብ አድርጎታል ነው ያሉት።

በመሆኑም ከመደበኛ ባሻገር ስብእና እና  መልካም እሴት ላይ መሰረት ያደረጉ ተጨማሪ ካሪኩለም ያስፈልጋል ብለዋል። 

የመደመር ትውልድ መጽሃፍ አገሩን የሚያውቅ ትውልድ በመፍጠር ረገድ አዲስ አካሄድ የሚያመላክት መሆኑን ጠቅሰዋል። 

የነገዋን ኢትዮጵያ የተሻለ የማድረግ ሃላፊነት ያለበት የአሁኑ ትውልድ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የስነልቦና ባለሙያዋ ሰብለ ሃይሉ ናቸው።


 

የአሁኑ ትውልድ ቁርሾን በማስወገድ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርና ትብብርን ማሻገር አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ባምላክስራ ፋሲል ትውልዱን በተሻለ አግባብ ለመቅረጽ የእይታ (ፓራዳይም ለውጥ) ያስፈልጋል ብላለች።


 

ከዚህ አኳያ የመደመር ትውልድ መጽሃፍ እኔ እና እኩዮቼን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አካታችና አዲስ የትውልድ ቀረጻ እይታ ያለው ነው ብላለች።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም