በሲዳማ ክልል የልዩ ኃይል አደረጃጀታዊ መዋቅርን የማስፈጸም ሥራ የመጨረሻው ምዕራፍ ደርሷል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የልዩ ኃይል አደረጃጀታዊ መዋቅርን የማስፈጸም ሥራ የመጨረሻው ምዕራፍ ደርሷል
ሀዋሳ፤ ሚያዚያ 02/2015 (ኢዜአ):-.በሲዳማ ክልል በመንግሥት የተጠናው የልዩ ኃይል አደረጃጀታዊ መዋቅርን የማስፈጸም ሥራ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ ።
የቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ጢሞቲዎስ ለኢዜአ እንደገለጹት በመንግሥት የተጠናው የልዩ ኃይል አደረጃጀታዊ መዋቅር ጠንካራና ወጥ የሆነ አገራዊ የፀጥታ ተቋም ለመገንባት ያለመ ነው።
በክልሉም የልዩ ኃይል አደረጃጀታዊ መዋቅርን የማስፈጸም ስራን ከፌዴራልና ከክልል አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ሂደቱም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል ብለዋል።
የልዩ ኃይል አባላቱ በፍላጎታቸው ወደ መደበኛ ፖሊስ፣ ማረሚያ ኮሚሽን፣ ፌዴራል ፖሊስና ወደ አገር መከላከያ ሰራዊት የሚገቡትን የመለየት ስራ 95 በመቶ ተሰርቷል ነው ያሉት አቶ አለማየሁ።
አገር የደህንነትና ሉዓላዊነት አደጋ በተጋረጠባት ወቅት የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ለሀገር ሠላምና አንድነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
የክልሉን ልዩ ኃይል አባላት በፍላጎታቸው የአገር መከላከያ ሰራዊትን፣ የፌዴራል ፖሊስንና መደበኛ ፖሊስን እንዲቀላቀሉ ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።