በዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚታየውን የግብዓት እጥረት ለመፍታት የግሉ ሴክተር በቅባት እህል ምርታማነት ላይ በስፋት ሊሰማራ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚታየውን የግብዓት እጥረት ለመፍታት የግሉ ሴክተር በቅባት እህል ምርታማነት ላይ በስፋት ሊሰማራ ይገባል

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2015 (ኢዜአ)፦ በዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚታየውን የግብዓት እጥረት ለመፍታት የግሉ ሴክተር በቅባት እህል ምርታማነት ላይ በስፋት ሊሰማራ እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
የግብርና ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት የቅባት እህል አምራቾችን ከዘይት አምራቾች ጋር የሚያገናኘው የምክክር መድረክ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
መድረኩ የቅባት እህል ምርትና ምርታማነት ለመጨመር እና የግብዓት አቀራረብ ችግሮች ዙሪያ ተወያይቶ ለመፍታት እንዲሁም ትስስርን ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለሰ መኮንን በዚሁ ጊዜ የግብርና ዘርፉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለግብርና ማቀነባበሪያ የጥሬ ዕቃ ምንጭ በመሆን ለኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርት እድገትን ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለቅባት እህሎች ምርታማነት ምቹ የአየር ጠባይና ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህን በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የፋይናንስ እጥረት፣ የመሰረተ ልማቶች በሚፈለገው መጠን አለመስፋፈትና የግብርና ማካናይዜሽን አለመስፋፋት ለችግሩ ዋነኞቹ ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ይህን ለመፍታት የፖሊሲና አሰራር ሪፎርም ከማድረግ ባሻገር ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ ኢንሼቲቮችን በመተግበር ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያያትም በኢትዮጵያ ለቅባት እህል ምርታማነት ያለውን ምቹ ሁኔታ በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል እንሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ባለድርሻ ተቋማት ተቀናጅተውና ተናበው ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ይህም በዘይት ፋብሪካዎች የሚታየውን የግብዓት አቅርቦት ውስንነት ለመፍታት ያግዛል ብለዋል፡፡
በመድረኩ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዘይት ምርት ላይ የሚታየውን ግብዓት እጥረት ለመፍታት የአመራረት ዘዴውን ማዘመን እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በተለይ በዘርፉ የመካናይዝድ ልማት አንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ ባላሃብቶች በቅባት አህል ምርት ላይ በስፋት ሊሳተፉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ክልሎች በዘርፉ መሰማራት ለሚሹ ባለሃብቶች ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአኩሪ አተርና ሰሊጥ በማምረት በስፋት ከሚታወቁ የአፍሪካ አገራት አንዷ ናት፡፡
ለአብነትም በ2014/15 የምርት ዘመን በአገር አቀፍ ደረጃ በአኩሪ አተር ከለማ 340 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡