ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ የሚዲያ ነጻነትን በኃላፊነት መንፈስ ሊጠቀሙ ይገባል

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2015 (ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ የሚዲያ ነጻነትን በኃላፊነት መንፈስ ሊጠቀሙ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) "መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም፣ ለዴሞክራሲ ስርዓትና የሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና በሚመለከት የውይይት መነሻ ጹህፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ ዓለም፣ መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠርና የአገርን ጥቅም በማስከበር ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃንን ሚና በተገቢው አግባብ በመጠቀም ረገድ ከፍተቶች መኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡

መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ አደጋ የሚጥሉ የውስጥ ችግሮችን ከማባባስ ሊቆጠቡ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ኢትዮጵያን በትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባች አገር መሆኗን አስታውሰው፤ የአሁኑ ትውልድም አገሩን በታላቅ የኃላፊነትና የቅንነት መንፈስ ለመለወጥ መስራት ይገባዋል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙሃን በኃላፊነት መንፈስ በአገር ግንባታ ሂደት ላይ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በመድረኩ መገናኛ ብዙኃን ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ በሚመለከት የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የአሃዱ ራዲዮና ቴሌቭዥን ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፤ የመረጃ ነፃነት ከዴሞክራሲ መገለጫዎች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን መገናኛ ብዙሃን ነጻነትን፣ የአገርንና ህዝብ ጥቅምን ባከበረ መልኩ መጠቀም እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ፤ መገናኛ ብዙኃን የተሳሳቱ አካሄዶችን በመጠገን ለአገር ሰላምና ደህንነት ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ለሰላም ግንባታ ሂደት የሚጠበቅባቸውን ገንቢ ሚና መጫዎት ካልቻሉ በአገርና ህዝብ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም፡፡


 

በውይይቱ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር)፤ መገናኛ ብዙኃን መንግስትና ህዝብን በማገናኘት የዜጎች ድምጽ ሆነው የማገልገል ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በዚህም በአገር ግንባታ ሂደት ላይ ህዝብና መንግስት ተቀራርበው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠርም እንዲሁ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንድሞ፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማሳወቅ ረገድ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ተቋማቱ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር ተቀራርበው በመስራት ሙያዊ ክህሎታቸውን ማሳደግ አለባቸው ነው ያሉት፡፡

የአገርን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቀው እንዲያስቀጥሉም የኢትዮጵያን ፍላጎት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች በማሳወቅ ረገድ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ትውልዱን በአገር ፍቅር፣ ዴሞክራሲና ሰላም እሴቶች መገንባት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ዶክተር ዮናስ አዳዬ ናቸው፡፡

በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን የአገር ጥቅምና የትውልድ ግንባታ ላይ ያላቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአገርን ብሔራዊ ጥቅም፣ ዴሞክራሲ እና የሰላም ግንባታን ለማስቀጠል የትውልድን የአስተሳሰብ ክህሎት ማጎልበት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለተለያየ ዓላማ የተቋቋሙ የመገናኛ ብዙኃን በተቀራራቢ ብሔራዊ ትርክት ላይ መስራት ከቻሉ ለአገር ግንባታ ስራ ገንቢ ሚና ይጫዎታሉ ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እንድሪስ ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ ዓለም፤ ለተነሱ ሃሳቦች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የአገርን አንድነት ለማስቀጠል በትውልዱ ላይ የአእምሯዊ ልማትን በትኩረት መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።


 

የአሃዱ ራዲዮና ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፤ ለፖለቲካ ጥቅም ብቻ የሚሰሩ ማህበራዊ አንቂዎች እየበዙ መምጣት የመገናኛ ብዙኃንን ሚና ወደ መቆጣጠር እንዲያመሩ እያደረገ ነው ብለዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪው ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ለትውልድ የሚበጅ ተሻለ የትምህርት ስርዓት ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በመረዳት መረጃ መስጠት የሚያስችል የመገናኛ ብዙኃንና የኮሙየኒኬሽን ምህዳር በመፍጠር ለአገር ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ማዋል እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም