ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል የልዩ ኃይሉ መልሶ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ ነው--የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን 


ሀዋሳ ሚያዚያ 2/2015 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ክልል በመንግሥት በተጠናው መሰረት ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዓለማየሁ ማሞ አስታወቁ። 

ወጥ የሆነ የጸጥታ ሀይል ማደራጀቱ ተገቢ መሆኑንም ኮሚሽነር ዓለማየሁ ማሞ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በመንግሥት የተጠናው የልዩ ኃይል አደረጃጀታዊ መዋቅር በክልሉም ህገ-መንግስታዊ አሰራርን በጠበቀ መልኩ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ልዩ ኃይሉ በብሄርና ክልል የተዋቅረ ስለነበር የመደበኛ ፖሊስ ተግባርን በእጅጉ ያዳከመ ሆኖ መቆየቱንም አስታውሰዋል።


በክልሉ አንዳንድ አካባቢ አጋጥሞ የነበረውን የፀጥታ ችግር የክልሉ ልዩ ኃይል ብቻውን እንዳልፈታ ገልጸው፤ በየአካባቢው ህዝብ ለፌዴራል ፖሊስና ለመከላከያ ሠራዊት ያለው ፍላጎት ሲታይ ውሳኔው ተገቢ ነው ብለዋል።


ኮሚሽነር አለማየሁ አክለውም የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት በተቀመጠው አማራጭ መሰረት በፍላጎት መርጠው ድልድሉ መጠናቀቁን ገልጸው የማደራጀቱ ስራ መቀጠሉን ተናግረዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም