ለትንሳኤና የኢድ በዓላት የፍጆታ ምርቶች በሁሉም አካባቢ በቂ አቅርቦት አለ- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለትንሳኤና የኢድ በዓላት የፍጆታ ምርቶች በሁሉም አካባቢ በቂ አቅርቦት አለ- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2015(ኢዜአ)፦ ለትንሳኤና ኢድ በዓላት የፍጆታ ምርቶች በሁሉም አካባቢ በቂ አቅርቦት ማቅረቡን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።
የትንሳኤ በዓል በሳምንቱ መጨረሻ የሚከበር ሲሆን የኢድ በዓል ደግሞ በቀጣዩ ሳምንት የሚከበር ይሆናል።
በመሆኑም ከበዓላቶቹ አከባበር ጋር ተያይዞ በምርት አቅርቦት ዙሪያ የተደረገውን ዝግጅት በማስመልከት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ፤ በተከታታይ ሳምንታት በሚከበሩት የትንሳኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት የግብርና ምርቶችና የሸቀጦች አቅርቦት በስፋት መኖሩን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ላለፉት 20 ቀናት በክልሎች ከሚገኙ የንግድ ቢሮ አካላት ጋር በመነጋገር የምርት አቅርቦት በስፋት እንዲኖር በመደረጉ ሕብረተሰቡ በተረጋጋ መልኩ መሸመት ይችላል ነው ያሉት።
በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ በመግባት የተለያዩ ሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ የሚገኙ አካላት ካሉ በሕግ ተጠያቂ የሚደረጉ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አብዲ ኡመድ፤ የግብርና ምርቶች፣ የእንስሳት ተዋጽኦና ሸቀጦች ጭምር በሕብረት ሥራ ማኅበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የሕብረት ሥራ ማኅበራትን ሳያካትት ሌሎች 30 በሚጠጉ የሕብረት ሥራ ማኅበራት ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን የሚያቀርቡ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የሕብረት ሥራ ማኅበራት የግብርና ምርቶችን፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ዱቄትና ሌሎችም ምርቶችን ለሸማቾች ማዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።
የሕብረት ሥራ ማኅበራቱ የእርድ እንስሳትን ጭምር ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውም ታውቋል።