አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከግዙፉ የቻይና ሲሚንቶ አምራች ኩባንያ ሲኖማ ኢንተርናሽናል ሊቀ-መንበር ሊዎ ያን ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከግዙፉ የቻይና ሲሚንቶ አምራች ኩባንያ ሲኖማ ኢንተርናሽናል ሊቀ-መንበር ሊዎ ያን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2015(ኢዜአ)፦ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከግዙፉ የቻይና ሲሚንቶ አምራች ኩባንያ ሲኖማ ኢንተርናሽናል ሊቀ-መንበር እና የሲ ኤን ቢ ኤም ኩባንያ ዋና ዳይሬክተር ሊዎ ያን እና የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ቤጂንግ በሚገኘው የኩባንያው ዋና ጽህፈት ቤት ተወያይተዋል።
አምባሳደር ተፈራ በውይይቱ ወቅት ሲኖማ ኢንተርናሽናል ኩባንያ በኢትዮጵያ የሲሚኒቶ ፋብሪካዎች ላይ ከዲዛይን ጀምሮ በግንባታ ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነው በኢትዮጵያ ካለው የግንባታ ስፋት አንጻር የሲሚንቶ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ተፈራ አያይዘውም ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የሲሚንቶ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት በዘርፉ ኢንቨስት በማድረግ ቢሰማራ የጋራ ተጠቃሚነቱ ሰፊ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የሲኖማ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ሊቀ-መንበር ሊዎ ያን በበኩላቸው ዘመኑ ያፈራውን ምርጥ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽእኖ የማይኖረው ፋብሪካ በኢትዮጵያ ለመገንባት ሃሳብ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
አምባሳደር ተፈራ በአዲስ አበባ ከሚያዚያ 18 –20/2015 በሚካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ኩባንያው እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ኩባንያው በኤምባሲው የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ የሚሳተፍ ቡድን እንደሚልኩ መግለጻቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማህበራዊ ትስስር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።